ኮሌጆቹ የተፈጥሮ ሃብታቸውን በሚያለሙ ስልጠናዎች ላይ እንዲያተኩሩ ተጠየቀ

607

አሶሳ የካቲት 21/2011 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተፈጥሮ ሃብታቸውን በሚያለሙ የሥልጠና ዘርፎች እንዲያተኩሩ የፌዴራል ቲክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ አሳሰበ።

በአሶሳ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ ቴክኒክ ኮሌጆች ቡድን መሪዎች የተዘጋጀ ስልጠና ተጀምሯል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐብታሙ ክብረት በስልጠናው ላይ እንደተናገሩት ክልሎች የተፈጥሮ ሃብታቸውን ለኢንዱስትሪ ግብዓቶች በሚጠቀሙና በጥናት የተለዩ የስልጠና ዘርፎች ላይ ያተኮረ የሰው ኃይል ማምረት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በክልሉ ያሉት ኮሌጆች የተፈጥሮ ቀርከሃና ማዕድናትን በማልማት ስልጠና ቢሰጡ ከክልላቸው አልፈው ለአገሪቱ ኢንዱስትሪ ልማት ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ የሚገኙት 462  ኮሌጆች በግብርና፣ በጤና፣ በመንገድ፣ በብረታ ብረትና እንጨትና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ባለሙያዎች እንደሚያሰለጥኑ አቶ ሐብታሙ አመልክተዋል።

ሆኖም የባለሙያዎቹ ብቃት ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በሚያስፈልገው የሰው ኃይል ብቃት ፍላጎት ልክ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ  ኮሌጆቹ ከኢንዱስትሪና ከተቋማት ጋር በመቀናጀት የዕውቀትና የልምድ ማዕከል ብቻ መሆን ሲገባቸው የብቃት ምዘናን ደርበው እየሰሩ ነው፡፡

ኤጀንሲው በኮሌጆቹ የሚታዩ ችግሮች ላይ ያተኮረና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ መሆኑንም  አስታውቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቃሲም ኢብራሂም በክልሉ ዘርፉን ለማሻሻል የ100 ቀናት ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በተደራጀ መልኩ መስጠት የተጀመረው ባለፉት 11 ዓመታት ነው።