በዞኑ የተመረተ ከ36ሺ ኩንታል በላይ ዓሳ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ቀረበ

60
ጎንደር ግንቦት 21/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተመረተ ከ36ሺ ኩንታል በላይ እርጥብና ደረቅ ዓሳ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ መቅረቡን የዞኑ የእንስሳት ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የእንስሳት እርባታ ተዋጽኦና መኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ መንገሻ መኳንት ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ተመርቶ  ለገበያ የቀረበው ይሄው ዓሳ ህጋዊ የንግድ ፍቃድ ባለቸው 91 ነጋዴዎችና ማህበራት አማካኝነት  ነው፡፡ በጎንደር ዙሪያ ፣ምዕራብና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች 822 አባላት ያሏቸው አራት አሳ  አስጋሪ  ማህበራት ከ34ሺ ኩንታል በላይ እርጥብ ዓሳ ለጎንደርና ለባህርዳር ከተሞች ገበያ አቅርበዋል፡፡ በዓሳ ንግድ ስራ የተሰማሩ ነጋዴዎች በበኩላቸው 2ሺ ኩንታል በጸሃይ ኃይል የደረቀ አሳ በመተማና ሁመራ በኩል ለሱዳን ገበያ አቅርበዋል፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከዞኑ ለማቅረብ የታቀደው ከ70ሺ ኩንታል በላይ እንደነበር ያስታወሱት ቡድን መሪው በገበያ እጦት፣ በምርት ጥራት መጓደልና በዘመናዊ የዓሳ ማምረቻ መሳሪያዎች አለመኖር እቅዱን ማሳካት እንዳልተቻለ ነው ያመለከቱት፡፡ በዞኑ ንግድ መምሪያ የእንስሳት ተዋጽኦ ግብይት አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ ሙሉ እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረበው እርጥብ ዓሳ ከ238 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ለሱዳን ከገበያ ከቀረበው ደረቀ ዓሳ ደግሞ 100ሺህ ዶላር የውጪ ምንዛሬ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ " በሱዳን ያለው የደረቀ ዓሳ ገበያ እየተቀዛቀዘ መጥቷል"  ያሉት ደግሞ ደረቀ ዓሳን ለሱዳን ገበያ የሚያቀርቡት አቶ እስጡፋኖስ አየለ ናቸው፡፡ ባለፉት ዘጠኝ  ወራት 110 ኩንታል ደረቅ ዓሳ ለሱዳን ገበያ በማቅረብ 5ሺህ 500 ዶላር ለሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ጯሃይት ከተማ የተቋቋመው አቡኑና አለም የዓሳ አስጋሪዎች ማህበር 30 ኩንታል እርጥብና ደረቅ ዓሳ በማምረት ለገበያ ማቅረቡን የማህበሩ ሊቀ-መንበር አቶ አቡኑ ደሴ ተናግረዋል፡፡ አምስት አባላት ያሉትና ዘንድሮ ባገኘው የ315ሺ ብር ብድር በጣና ሀይቅ ላይ የዓሳ ማስገር ስራ ላይ የተሰማራው ማህበሩ ከምርቱ ሽያጭ ባለፉት ወራት 70ሺ ብር ገቢ ማግኘቱንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም