በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ምሽት ሊዘጋጅ ነው

88

አዲስ አበባ የካቲት 20/2011 አረንጓዴና ንጹህ አዲስ አበባን በመፍጠር መዲናዋን የከተማ ቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ዓላማ ላለው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ምሽት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደሚዘጋጅ ተጠቆመ።

"ለሸገር ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ገበታ ይቅረቡ" በሚል መሪ ሃሳብ ለአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ እራት ላይ ለአንድ ገበታ 5 ሚሊዮን ብር ተቆርጦለታል።

የቢዝነስ ባለቤቶች፣ የኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በገበታው ላይ ለመቅረብ ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት አድራሻ ይፋ ሆኗል።

በዚሁ መሰረት ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ለመደገፍና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር ገበታ ለመቅረብ sheger@pmo.gov.et ላይ ፍላጎት መግለጽ እንደሚቻል ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ የሚተገበረው የአዲስ አበባን ዋና ዋና ወንዞች ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት 29 ቢሊየን ብር እንደሚፈጅ ተገልፆ ነበር።

በአዲስ አበባ ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ላይ የሚደረገው ተሳትፎ ለቀጣይ ትውልድ ውብ ከተማ ማስተላለፍ በዋጋ እንደማይተመን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት በእራት ግብዣው ላይ እንዲገኙ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከእንጦጦ እስከ ቃሊቲ የሚደርሰው ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት 56 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል።

በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ፕሮጀክቱ ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።

የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የአዲስ አበባን የነፍስ ወከፍ የአረንጓዴ ሽፋን ከተቀረው የአፍሪካ አካባቢ ጋር ሲነጻጸር ከነበረበት ዜሮ ነጥብ ሦስት ሜትር ኪዩብ ወደ ሰባት ሜትር ኪዩብ ከፍ ያደርገዋል።

በተለይ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን እንዲሁም የእረፍተ ጊዜ ማሳለፊያ ስፈራዎችን በማዘጋጀት የውጪና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመሳብ እንደሚያስችል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

በወንዞቹ ዳርቻና ሕዝብ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች የአገልግሎት ዘርፉን በማበረታታት ካፌዎች፣ ምግብ ቤቶች እንዲስፋፉ እድል እንደሚሰጥ ነው የተጠቆመው። ለከተማ አስጎብኚዎች አገልግሎት ማመቻቸት ከውጤቶቹ መካከል ተጠቃሽ ነው።  

ወደ ወንዞቹ የሚቀላቀሉ ፍሳሽ ቆሻሻዎች አቅጣጫቸው ተቀይሮና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታክመው በዳርቻዎቹ የሚተከሉ እጽዋቶችን ለማጠጣት እንደሚውሉም ተገልጿል።

በዝናብ ጊዜ የሚፈጠር ጎርፍ ወደ ወንዞቹ እንዳይገባ በዳርቻዎቹ የማፋሰሻ መስመር እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ የብስክሌት መስመር፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ  አቅርቦትና የመናፈሻ አገልግሎትን የያዘ ሲሆን፤ በዋናነት ከፀሀይ የሚመነጭ ታዳሽ ሃይልን ይጠቀማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም