የኢትዮጵያ ምግብ፣ መድሃኒትና ቁጥጥር ባለስልጣን አሰራሩን የሚያዘምን ዘዴ ይፋ አደረገ

186

አዲ አበባ የካቲት 20/2011 የኢትዮጵያ ምግብ፣ መድሃኒትና ቁጥጥር ባለስልጣን አሰራሩን የሚያዘምንና በቴክኖሎጂ የሚደግፍ ዘዴ ይፋ አደረገ። 

ቴክኖሎጂው ህገ-ወጥ የመድሃኒት ዝውውር፣ የመድሃኒት አምራቾችና አቅራቢዎችን ህጋዊ መስፈርትና ሌሎች ውስብስብ አሰራሮችን በማስቀረት ፈጣንና ዘመናዊ አሰራርን የሚዘረጋ ነው ተብሏል።

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በዚሁ ግዜ እንደገለጹት ቀደም ሲል ባለስልጣኑ በእጅ የታገዘ አሰራርን በመከተሉ ከፍቃድ አሰጣጥ፣ አቅራቢዎችንና ህገ ወጥ የመድሃኒትና የምግብ ምርቶችን ከመቆጣጠር አኳያ ክፍተቶች ነበሩበት።

በዚህም የመድሃኒት፣ የምግብና የመዋቢያ ዕቃዎች አስመጪዎች በውስብስብ አሰራር ምክንያት ቅሬታዎችን ሲያሰሙ መቆየታቸውንና ይህም ለህገ ወጥ ንግድ በር የከፈተ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም መስሪያ ቤቱ እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለማስቀረት የሚያግዘውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መተግበር አስፈላጊ ሆኗል።

"Electronics Regulatory Information System/ERIS/ " የተሰኘና ኢንተርኔትን ብቻ በመጠቀም ምርቶችን ወደአገር ውስጥ የሚያስገቡ አቅራቢዎች የሚመዘገቡበትና የብቃት ማረጋገጫ የሚያገኙበት አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል።

ሶፍትዌሩ ምርቶችን ወደ አገር ለማስገባት፣ ፍቃድ ለማውጣት፣ መድሃኒትን ለማስመዝገብና በአቅራቢውና በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መካከል ያለውን ውስብስብ አሰራር የሚያስቀር ነው ብለዋል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ሙከራ ሲደረግበት የነበረው ይህ ሶፍትዌር ውጤታማነቱና አስፈላጊነቱን ከግምት በማስገባት ከዛሬ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ላይ የሚውል እንደሆነም አክለዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄራን ገብራ በበኩላቸው እንደገለጹት መድሃኒቶችን፣ የተቀነባበሩ ምግብና መጠጦችን፣ የውበት መጠበቂያዎችን እና ሌሎች ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ አቅራቢዎች ምርታቸውን ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ በነበረው ሂደት የቀደመው አሰራር አሰልቺና ውስብስብ ነበር።

በዋነኝነትም ወረቀትን መሰረት ያደረገ አሰራር መከተላቸው ለሰነዶች መጥፋት፣ የአቅራቢዎች መረጃ አቀማመጥ ችግር፣ ለብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አሰጣጥ መዘግየት፣ ለምርት ልየታ ሥራ ከፍተኛ ክፍተት ሲፈጥር እንደነበር አስታውሰው በዚህም ሙሉ ለሙሉ ደህንነቱና ወቅቱን የጠበቀ ምርት ተደራሽ ለማድረግ አዳጋች ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

ክፍተቶቹን ተከትሎ ምርቶች ወደ ህብረተሰቡ ከመድረሳቸው በፊት በሚደረገው ቁጥጥር ችግሮች በመገኘታቸው እንዲወገዱ አሊያም እንዲመለሱ እየተደረገ አገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጋት እንደነበርም ገልጸዋል።

በዋናነትም ህገ-ወጥ የምግብና የመድሃኒት ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሶፍትዌሩ የጎላ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

በተጨማሪም ከአቅራቢ ድርጅቶች ባሻገር ከመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ጋር ሶፍትዌሩ የተሳሰረ በመሆኑ ኤጀንሲው የህክምና መሳሪያና መድሃኒቶችን በግዥ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ በቀላሉ ግዥው እንዲከናወን ያግዘዋል ብለዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስካሁን ከ21 ሺህ በላይ ምርቶችን በመመርመር ማረጋገጫ የሰጠ ሲሆን ከ30 በላይ የሚሆኑ አምራቾች ላይ ደግሞ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን  ከጤና ሚኒስትሩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም