የሐሳብና የፖለቲካ ልዩነቶችን እንደውበት በመውሰድ ለህዝብ ጥቅም በጋራ መስራት አለብን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ

124
ባሌ ሚያዝያ 27/2010 የሐሳብና የፖለቲካ ልዩነቶችን እንደውበት በመውሰድ ለህዝብ ጥቅም በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ  በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ መዳወላቡ ስታዲየም ተገኝተው ለሮቤ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ “የህዝብ ትግልን ባስጀመረን የታጋይና ጀግኖች ሀገር ባሌ ተገኝተን ከህዝብ ጋር መወያየት በመቻላችን ኩራት ተሰምቶኛል” ብለዋል። የሐሳብና የፖለቲካ ልዩነት እንደውበት ተወስዶ በህዝብ ጥቅም ላይ ተግባብቶ  መስራት ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ መሆኑንም በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተውታል። "ጊዜው ወጣቶችና ቀሪው የህብረተሰብ አካል ከችግር የምንሸሽበት ሳይሆን ሰርተን የምንለወጥበት ያለእረፍት በመስራት ድህነትን የምናሸንፍበት ጊዜ ነው" ብለዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሌ ጉብኝት አስቀድሞ ስምንተኛው የኦሮሚያ ክልል የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ኤግዚቢሽንና ባዛር ለአምስት ቀናት ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና አመራሮቹ በተገኙበት በ26 ዘርፎች  ለተደራጁ አንድ ሺህ 127 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝነት የማሸጋገር ፕሮግራም  ተካሂዷል፤ የተሻለ ስራ ለፈጸሙትም የእውቅናና ተሰጥቷል። ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራቱ በስራቸው ለ4 ሺህ 287 ዜጎች የስራ እድል የፈጠሩ ሲሆን ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት የሮቤ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎችን በሮቤ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ በማወያየት ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም