በጌዴኦ የ "ዳራሮ " በዓል ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

69

ዲላ የካቲት 20/2011 የጌዴኦ  ዘመን መለወጫ የ"  ዳራሮ  " በዓልን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ ገለጹ፡፡

በዓሉ "ባህላዊ እሴቶቻችን ለሠላማችንና ሀገራዊ አንድነታችን " በሚል  ከመጋቢት 4/2011ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት በዲላ ከተማ ይከበራል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው  እንዳሉት ዘንድሮ የሚከበረው ይሄው በዓል ምክንያት በማድረግ የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም ፣  የባህላዊ ምግብና መጠጥ ፣ የሥዕልና የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እንዲሁም  የንግድ ትርኢት ይካሄዳል፡፡

በዓሉ ለጌዴኦ ህዝብ የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን የምስጋና፣ የይቅርታ ፣  የሠላም አስተምህሮቶች ከአባቶች ወደ ልጆች የሚተላለፉበትም ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በበዓሉ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እንዲሳተፉ ፤በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆችም እንዲታደሙ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የጌዴኦ ህዝብ " ዳራሮ" ን ጨምሮ ለአረንጓዴ ልማት ተምሳሌት የሚሆን የጥምር ግብርና ዜዴ ፤ የትክል ደንጋዮችና ሌሎች ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች እንዳሉት የገለጹት አቶ ገዙ በበዓሉ ላይ እነዚህን እሴቶች የማስተዋወቅ ሥራም እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

" የጌዴኦን ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ  ለቀጣዩ ትውልድ በተገቢው መንገድ ለማስተላለፍ የበዓሉ አከባበር የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው " ብለዋል፡፡

የዞኑ ባህል ፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አሰፋ በበኩላቸው ሁሉም ህብረተሰብ ስለበዓሉ ዕውቀት እንዲኖረውና ከወትሮው በተሻለ ድምቀት እንዲያከብረው በወረዳዎች  የህዝብ ንቅናቄ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዛፎችን የመንከባከብና እንዳይቆረጡ የመጠበቅ እሴት የሆነው የጌዴኦ "  ባቦ" ሥርዐት ፣ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ከሌሎች ጋር የመኖር የአብሮነት እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የጌዴኦ አባገዳ ዳምቦቢ ማሮ   የዳራሮ  በዓል  " ስላለፈው ዓመት እንዲሁም ስለሰጠን በረከት ፈጣሪን የምናመሰግንበት መጪውንም ዓመት እንዲባርክልን የምንለምንበት ነው" ብለዋል ፡፡

በዓሉ የይቅርታና የዕርቅ በመሆኑ ለሠላም ያለው አስተዋፅኦ  ከፍተኛ እንደሆነና የአባቶች ነባር ዕውቀት ለልጆች የሚተላለፍበት ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም