14 ቢሊዮን ብር የሰወሩ 135 ድርጅቶች እርምጃ ተወሰደባቸው -ገቢዎች ሚኒስቴር

148

አዲስ አበባ የካቲት 20/2011 ህግን ለማስከበር ባደረገው የዘመቻ ሥራ 14 ቢሊዮን ብር የታክስ ስወራ ፈጽመው ባገኛቸው 135 ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በመጀመሪያውና በሁለተኛው የ100 ቀናት እቅድ የ ህግ ማስከበር ሂደትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አበቤ እንደገለጹት፤ በመጀመሪያውና በሁለተኛው የመቶ ቀናቶች ውስጥ ህግ ለማስከበር የሚያስችል ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህም በህብረተሰቡ ጥቆማ፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክትትል ሥራና የደረሰኝ ኦዲት ምርመራ መሰረት በማድረግ 14 ቢሊዮን ብር የታክስ ስወራ በፈጸሙ 135 ድርጅቶች ላይ  አስዳደራዊ ቅጣትና በመደበኛ የህግ አግባብ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው 100 ቀናት እቅድ በተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሳይቆርጡ የሰበሰቡትን ታክስ ለግል ጥቅማቸው ካዋሉ 55 ድርጅቶች ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታ የሚገኙ 64 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሁለተኛው የ100 ቀናት እቅድ ደግሞ ሽያጭ በሚያከናውኑበት ወቅት ደረሰኝ በማይቆርጡ 23 ድርጅቶች ላይ በተሰራው የህግ ማስከበር 41 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

በተደረገው ኦፕሬሽን የጅምላ ነጋዴዎች፣ አከፋፋዮች፣ የአንደኛ ደረጃ ተቋራጮች፣ አምራቾችና ቸርቻሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህም በተደጋጋሚ ተመላሽ በመጠየቅ፣ ግብር ሲያሳውቁ ምንም እንዳልሰሩ ባዶ በማሳወቅና ደረሰኝ የማይቆርጡ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የታክስ ስወራ ግለሰቦች እንዲከብሩበትና አገር ማግኘት የሚገባትን ገቢ የሚያስቀር ሲሆን ይህ ተግባር እንዲቀር የሚሰራው ስራ በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስምረውበታል።

የንግዱ ማህበረሰብ ግብር በወቅቱ አሳውቆ ያለመክፈልና ትክክልኛውን ገቢ ያለማሳወቅ ወንጀል መሆኑን አውቆ በወቅቱ እንዲከፍል በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለው የግብር ንቅናቄ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ወይዘሮ አዳነች አብራርተዋል።

በተለይም በህጋዊ መንገድ ደረሰኝ መቁረጥ፣ ደረሰኝ እንዲቆረጥለት የመጠየቅ፣ ግብር ከፋዩ የንግዱ ማህበረተሰብ በወቅቱ ማሳወቅ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ካመጣባቸው መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም