ለኢትዮጵያዊ አንድነት መጎልበት ሁሉም በቅንነት ሊሰራ ይገባል-ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

81

ደሴ የካቲት 20/2011 ለአዲሱ ትውልድ ትክክለኛውን ታሪክ በማስተማር ለኢትዮጵያዊ አንድነት መጎልበት ሁሉም በቅንነት ሊሰራ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

123ኛውን የአደዋን የድል በዓል በቦታው ለማክበር የሚጓዘውና ከሁሉም ክልሎች የተወጣጣው የልኡካን ቡድን በደሴ ከተማ በመገኘት ታሪካዊ ቦታዎችን ጎብኝቷል፡፡

በሚኒስቴሩ የባህል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በእለቱ እንዳስታወቁት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትክክለኛውን ታሪክ ሊያውቅና ባለቤትነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል።

የአድዋ የድል በዓል ሲከበርም አንድነትንና ሰላምን በመዘከር እንዲሁም የመቻቻል ባህልን በማጠናከር መሆን እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

“ድሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ህዝቦች ኩራትና አንድነት ኃይል መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው” ብለዋል።

127 አባላትን ይዞ ከአዲስ አበባ የተነሳው ቡድኑ በጉዞው የተለያዩ ታሪካዊ ቦታዎችን በመጎብኘት ”የአደዋ ድል የአንድነታችን ማህተም” በሚል መሪ ቃል 123ኛው የአደዋ የድል በዓልን በቦታው በመገኘት ያከብራል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ማህደር አራጌ በበኩላቸዉ “የአባቶቻችን ታሪክ ሳይበረዝ ለትውልዱ በማስተላለፍ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን እንዲጎለብት ብዙ መስራት ይጠበቅብናል”ብለዋል።፡፡

የዘንድሮ በዓል ሲከበር ኢትዮጵያዊያን ለውጭ ወራሪ እጅ ሳይሰጡ በአንድነትና በፍቅር ጸንተው በባህላዊ መሳሪያ ጠላትን ማንበርከካቸውን ገልጸው የንጉስ ሚካኤልን አይጠየፍ ቤተ-መንግስትና መርሆን ግቢን ጨምሮ ታሪካዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ መደረጉን ገልጸዋል።

የወሎ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን የአደዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑን ጠቅሰው አጼ ምኒሊክ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በወረኢሉ ከተህ ጠብቀኝ ያሉትን የአዋጅ ጥሪ ተቀብሎ ሀገሩን በአንድነት በመከላከል ድልን መጎናጸፉን ተናግረዋል።

“ይህን ታሪክ ደግሞ ትውልዱ አውቆ ለቀጣዩ እንዲያስተላልፍ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን ይወጣል” ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አስካል ተሰማ በበኩላቸው “በታሪክ የሰማሁትን በአካል ተገኝቼ በማየቴ ስለ አንድነት ጠንክሬ እንድሰራ በር ከፍቶልኛል” ብለዋል።

“ወጣቱ ትክክለኛውን ታሪክ ተረድቶ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት በመጠበቅ የአባቶቹን አደራ እንዲወጣ በቅንጅት እንሰራለን”ም ብለዋል።

ልዑኩ ዛሬ በውጫሌ ይስማ ንጉስ ታሪካዊ ቦታዎችን በመጎብኘት ወደ ወልድያ ይሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም