ቢሮው ከአድዋ ታሪክ ጋር የተያያዙ ስፍራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

700

አዲስ አበባ የካቲት 20/2011 ከአድዋ ጦርነትና ድል ጋር የተያያዙ ታሪካዊ ስፍራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የፌዴራልና የክልል የባህልና ቱሪዝም አመራሮችና ባለሙያዎችን እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃንን ያካተተ ልዑክ “ከሸዋ እስከ አድዋ” በሚል መሪ ቃል ታሪካዊ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ልኡል ዮሃንስ በዚህ ወቅት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ክልሉ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅና ለትውልድ ለመዘከር ብቻ ሳይሆን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው።

ልዑኩ በዛሬው እለት በደቡብ ወሎ የሚገኙና ከአድዋ ድል ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ታሪካዊ ስፍራዎችን እየጎበኘ ነው።

ክልሉ በሰሜን ሸዋ የሚገኘውን የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የትውልድ ስፍራ አንጎለላ እና የአንኮበር ቤተ መንግስት እንዲሁም ወረ-ኢሉ የውጫሌ ውል የተፈረመበትን የይስማ ንጉስ ታሪካዊ ስፍራዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ነው።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሱሌይማን እሸቱ በበኩላቸው ዞኑ የበርካታ ታሪካዊ ስፍራዎች ባለቤት መሆኑንና ቦታዎቹን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአድዋን ጦርነት የክተት አዋጅ የታወጀበትን የይስማ ንጉስ ታሪካዊ ስፍራና የወረ-ኢሉ ከተማን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በ25 ሚሊዮን ብር የሙዚየም ግንባታ መጀመር በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በጉብኝቱ የአድዋ ድል እንደሚዘከር ገልጸዋል።

ከአድዋ ታሪክ ጋር የተያያዙ ስድስት ታሪካዊ ስፍራዎችን በመጎብኘት ቦታዎቹን ለቱሪስት መዳረሻነት ለማልማት የመነሻ እቅድ ለማዘጋጀት የሚያግዝ ግብዓት እንደሚሰበሰብበትም ጠቁመዋል።

“አድዋ የአንድነታችን ማህተም” በሚል መሪ ሃሳብ የሚዘከረው 123ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ የአባቶችን አንድነት ለማሳየትና ታፍራና ተከብራ የቆየችውን አገር በአብሮነት ለማስቀጠል መነቃቃት ለመፍጠር በሚያግዝ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።