ትውልዱ በአድዋ ጦርነት አባቶቹ ያሳዩትን አንድነት በማስቀጠል አገር የመገንባት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

81

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 በኢትዮጵያ አሁን ያለው ትውልድ አባቶች በአድዋ ጦርነት ወቅት የነበራቸውን የአንድነት ፈለግ በመከተል ለአገር ግንባታ ሊተጋ እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ።  

123ኛውን የአድዋ ድል ምክንያት በማድረግ ዝክረ አድዋ የኪነ ጥበብ ምሽት በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አዘጋጅነት በብሄራዊ ቲያትር ትናንት ምሽት ላይ ሲካሄድ በርካታ ቁጥር ያለው ታዳሚ ተሳትፏል።      

የቀደሙት አባቶች የውጭ ወራሪን ሲመክቱ የነበራቸውን ወኔና የአገር ፍቅር የሚያሳዩ ፉከራ፣ ሽለላና የባህል ጨዋታዎች መርሃ ግብሩን አድምቀውታል።    

የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን 'ዋ ያቺ አድዋ' የሚለው ግጥም በአርቲስት አለማየሁ ታደሰ አማካኝነት ለታዳሚያን የቀረበ ሲሆን አሁን ያለው ትውልድ ለአገር ፍቅር ያለውን ስሜት የሚዳስሱ የኪነ ጥበብ ሥራዎችም እንዲሁ ቀርበዋል።   

የታሪክ ምሁር ኃይለመለኮት አግዘው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አድዋ የሰፈር ጦርነት ሳይሆን ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካውያን ቀና ብለው እንዲሄዱ ያስቻለ ታሪካዊ ድል የተገኘበት ጦርነት ነው።    

''የአድዋ ድል የአፍሪካ ምልክት ነው'' የሚሉት ምሁሩ ጋናን ጨምሮ 17 የአፍሪካ አገሮች የሰንደቅ ዓላማ ቀለማቸው ከኢትዮጵያ እንዲወስዱ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህ ድል የተገኘው ከምስራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከደቡብና ከሰሜን ሳይቀር አባቶች ሳይከፋፈሉ ለአንድ ዓላማ በመዝመታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።

''አሁን ያለው ትውልድ አባቶቹ ያሳዩትን አንድነት በማስቀጠል አገር የመገንባት ኃላፊነት አለበት'' ብለዋል።

''ከዚህ በኋላ ወደ ፊት ነው ማየት ያለብን ወደ ኋላ ተመልሶ መሰዳደብ፣ መተቻቸት ትርጉም የለውም፤ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን እንዴት እንገንባ? ኢትዮጵያችን ምን መምሰል አለባት? በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ለቀጣዩ ትውልድስ የምናስተላልፈው የሚለውን ሁላችንም ልናስብበት ይገባል'' የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።    

በተለይ አሁን ወቅቱ አደገኛ ብሄርተኝነትና ጎጠኝነት የሚስተዋልበት መሆኑን ያነሱት አቶ ኃይለመለኮት ከዚህ አስተሳሰብ በመላቀቅ በአንድነት አገር የማቅናት ሥራዎች ላይ ማተኮር ተገቢ እንደሆነ አመልክተዋል።

በምሽቱ ላይ የኪነ ጥበብ ባለሙያው አርቲስት ሰርጸ ፍሬስበሃት በአድዋ ጦርነት ወቅት አዝማሪዎች ኢትዮጵያውያንን ለትግል በማነሳሳትና ወኔ ማምጣት ላይ የነበራቸውን ሚና የሚዳስስ ጸሁፍ አቅርቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም