ጨፌ ኦሮሚያ የህብረት ስራ ማህበራትን አዋጅ አፀደቀ

160

አዳማ የካቲት 20/2011 የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) በክልሉ ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆኑ የህብረት ሥራ ማህበራትን ለመፍጠር ያስችላል ያለውን አዋጅ አፀደቀ። 

ምክር ቤቱ ትናንት የጀመረውን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን በኦሮሚያ የህብረት ስራ ማህበራትን ለማስፋፋት ያስችላል ተበሎ በቀረበለት ረቂቅ አዋጅ ላይ በመምከር አዋጁ ሥራ ላይ እንዲውል አፅድቆታል።

በሀገር ደረጃም ሆነ በክልሉ እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ እርምጃዎችን በምጣኔ ኃብታዊ ዘርፍ መደገፍ እንዲቻል የህብረት ስራ ማህበራትን በአዲስ መልክ ማቋቋም አስፈላጊነት ላይ ምክር ቤቱ በስፋት መክሯል።

በፌዴራል ደረጃ ብቻ የነበረው የህብረት ስራ ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ክልሎች የደረሱበትን የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴ ለማስተዳደርና ለማስቀጠል በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ክልሉ በዘርፉ የራሱን አዋጅ ማውጣት አስፈልጎታል ነው የተባለው።

አዋጁም በምክር ቤቱ የገጠር ልማት ጉዳይና የአስተዳደርና ህግ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴዎች ከመከሩበት በኋላ እንዲጸድቅ ለጨፌው ቀርቧል።

በክልሉ የታወጀውን የምጣኔ ኃብት ልማት ንቅናቄ እውን ለማድረግ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በአገርና ዓለማቀፍ ገበያ ተደዳዳሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ ጠንካራ የህብረት ሥራ ማህበራት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለቸው ተጠቅሷል።

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከመከረ በኋላ የህብረት ስራ ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር  218/2011 ሆኖ እንዲፀድቅ ወስኗል።  

እንደ ጀርመንና ጃፓን የመሳሰሉ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው የብልጽግናቸው መሰረት የህብረተ ስራ ማህበራት መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ጉባኤው ሌሎች አዋጆችን ከማፅደቅ ባሻገር ልዩ ልዩ ሹመቶችን ይሰጣል ተብሎም  ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም