የወሊሶ ከተማን እግር ኳስ ክለብ ለማጠናከር ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ

60

አምቦ የካቲት 20/2011 የወሊሶ ከተማን እግር ኳስ ክለብ ለማጠናከር ሀገር አቀፍ የንግድ ትርኢት፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር በወሊሶ ከተማ ተከፈተ።   

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የወሊሶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የክለቡ ሰብሳቢ አቶ ኃይሌ ጉርሜሳ እንዳሉት ባዛሩ ከትናንት ጀምሮ ለአስር ቀናት ክፍት ሆኖ ይቆያል።

በባዛሩ ላይ ከህንድና ከቱርክ የመጡ ነጋዴዎችን ጨምሮ ከ150 በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ተሳትፈዋል።

በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከሚሳተፉት ነጋዴዎች፣ ከመግቢያ ትኬት ሽያጭና ከስፖንሰር ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡    

አቶ ኃይሌ እንዳሉት ከባዛሩ የሚገኘው ገቢ የከተማዋን ስፖርት ክለብ ያለበትን የፋይናንስ እጥረት ለማቃለልና ለማጠናከር እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የወሊሶ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ የሌለው እንደመሆኑ መጠን በሚገኘው ገቢ ለቡድኑ አሰልጣኝ ለመቅጠርና ጠንካራ አቅም ያላቸው ተጨዋቾችን ለመግዛት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ባዛሩ ክለቡን ከማጠናከር ባለፈ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ኤግዚቢሽንና ባዛሩን ታዋቂው የኦሮምኛ ዘፈኝ ድምጻዊ ዲናኦል ኩምሳን ጨምሮ የወሊሶ ወሌ ባንድና የወሊሶ የኪነት ቡድን ያደምቁታል ተብሎ ይጠበቃል።

የወሊሶ ከተማ ስፖርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘለለው አስረስ በበኩላቸው " የባዛሩ መዘጋጀት ለበርካታ ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ ያነቃቃል " ብለዋል፡፡  

የስፖርት ክለቡን ለማጠናከር አስተዳደሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ቢመድብም በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ክለቡ በሚፈለገው ደረጃ ሊጠናከር እንዳልቻለ አመልክተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ከባዛሩ የሚገኘው ገቢ የስፖርት ቡድኑን ከሌሎች አቻ ከተማ የእግር ኳስ ቡድኖች እኩል ተወዳዳሪ ለማድረግ አቅም የሚፈጥር ነው።

በባዛሩ ላይ ከተሳተፉት ነጋዴዎች መካከል ወይዘሮ ስንቅነሽ ግዛቸው ከአዲስ አበባ እንደመጡ ገልጸው በባዛሩም ብረታ ብረት፣ ማሽኖችንና የተለያዩ ዕቃዎችን ለሽያጭ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

"ያቀረብኳቸውን እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ  በመሸጥ የተሻለ ትርፍ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጊያለሁ" ብለዋል።

በወሊሶ ከተማ የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ተሾመ አስራት በበኩላቸው ኢግዚቢሽንና ባዛሩ በወሊሶ ከተማ ማግኘት የማይችሏቸውን የተለያዩ እቃዎችን ለማግዛት ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም