የደገህቡር ከተማ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነች

55

ጅግጅጋ የካቲት 19/2011 በሶማሌ ክልል የደገህቡር ከተማ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ተጠናቆ ዛሬ  ተመረቀ፡፡

ፕሮጅክቱ ከጅግጅጋ አንድ መቶ ስልሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በስተ ምስራቅ አቅጣጫ በምትገኘው ደገህቡር ከተማ የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ከጅግጅጋ ወደ ደገህቡር  ከተማ የተከናወነው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክቱን መርቀው የከፈቱት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስተፌ ሙሁመድ ናቸው፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የነዋሪዎችን የረጅም ጊዜ የኃይል አቅርቦት ችግር የሚፈታ ነው ።

በሌሎች የክልሉ ከተሞችም የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ፕሮጅክቶች ተቀርጸው በሂደት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመው የደገህቡር ከተማ ህዝብ በቀጣይም ያለባቸውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ይሰራል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ መርዓዊ አያሌው በበኩላቸው  ከተማዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነችው ለሦስት ዓመታት የተካሄደው ፕሮጀክት በመጠናቀቁ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ለተዘረጋው መሥመር 410 የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ኮንክሪት ምሶሶዎች ተከላ ተከናውኗል፡፡

አቶ መርዓዊ እንዳሉት ፕሮጅክቱ ከከተማው በ120 ስኩየር ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኙ ጉነገዳ፣ ደገህመዳው እና አዋሬ ለተባሉት የወረዳ ከተሞች  እንዲሁም ሁለት የገጠር ቀበሌዎች ጭምር ተጠቃሚ  የሚያደርግ ነው፡፡

የጅግጅጋ ደገህቡር መብራት ዝርጋታ ፕሮጅክት አስተባባሪ አቶ ካሳሁን ጉብል ፕሮጀክቱ  ዘጠኝ ሚሊየን ብር ወጪ እንደሆነበት ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በከተማው ለስድስት ሰዓት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የዲዚል ጀነሪተር ወደ ሀያ አራት ሰዓት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደገህቡር  የኤሌክትሪክ ኃይል የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት አበራ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ ለከተማዋ በጄኔሬተር በወር የሚወጣውን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የናፍታ ወጪ እንደሚያስቀርም አስታውቀዋል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኒመአ አብዲ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል የነበረው የኤሌክትሪክ  አገልግሎት ውስን በመሆኑ ከአካባቢው ከባድ ሙቀት ጋር ተያይዞ ውሃ አቀዝቅዘው ለመጠቀም ይቸገሩ እንደነበር ጠቁመው አሁን መፍትሄ በማግኘቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ መሀመድ ሀሰን የተባሉት ነዋሪ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ለ24 ሰዓት መሆኑ ቀደም ሲል የነበረባቸውን የኃይል አቅርቦት ችግር  በማስቀረት ለአካባቢው እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም