''እሥራኤል ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የምታደርገውን ድጋፍ ታጠናክራለች''-አምባሳደር ዋራፍ

75

ድሬዳዋ የካቲት 19/2011 እሥራኤል በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ድጋፏን እንደምታጠናክር  አምባሳደር ራፋኤል ዋራፍ ገለጹ፡፡

አምባሳደሩ በድሬዳዋ ''ፌር ፕላኔት'' የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር  በምሥራቅ  ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች ተመልክተዋል፡፡ የመሰክ ቀኑም ተከብሯል።

በኢትዮጵያ የእሥራኤል አምባሳደር ራፋኤል ዋራፍ ከጉብኝቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ድጋፏን ታጎለብታለች።

በተለይ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ  በአገሪቱ እንዲስፋፋ እገዛዋን ታደርጋለች ብለዋል፡፡

ድርጅቱ  ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመለወጥና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አበረታች  እንቅስቃሴ  በማድረግ ላይ መሆኑንም  ገልጸዋል፡፡

አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት  ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ፣ ፖለቲካዊና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጎልበት እንደምትሰራም አምባሳደር ዋራፍ አረጋግጠዋል፡፡

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት  ፕሮፌሰር ከበደ ወልደጻድቅ  በበኩላቸው ድርጅቱ  ያስተዋወቀው  ቴክኖሎጂ ከትንሽ መሬት ከፍተኛ ምርት የሚገኝበትና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ለረዥም ጊዜ ሳይበላሹ ለማቆየት እንደሚያስችል ተናግረዋል ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂውን እንደ አንድ የግብርና ፓኬጅ በመውሰድ በአገሪቱ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ  እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

''ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም እየተመካከረ ነው'' ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ መሐመድ አብዱላሂ ከአምስት ዓመታተ በፊት ጥቂት አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር፣መሬትና የውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ በማጣመር የተጀመረው ፕሮጀክት አሁን ከ980 አርሶ አደሮች በላይ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና እንዳረጋገጡበት ተናግረዋል፡፡

የቲማቲም፣ የሽንኩርትና የቃሪያ ምርጥ ዘሮችንና የቴክኖሎጂ ድጋፍ የተጠቀሙት አርሶአደሮች በአንድ ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት ከአንድ ጊዜ ምርት እስከ 50 ሺህ ብር እያገኙ መሆናቸውንም ለአብነት አቅርበዋል፡፡

ቢሮው ሥራውን በ4ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ በማስፋፋት ዘጠኝ ሺህ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራሁ ነኝ ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም