ትምህርት ሚኒስቴር ለአዲሱ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ከ14 ሚኒስቴሮች ግብዓት ማሰባሰቡን ገለጸ

72

አዲስ አበባ የካቲት 19/2011 የትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ከ14 ሚኒስቴሮች ግብዓቶችን ማሰባሰቡን  ለኢዜአ ገለፀ።

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌጤ ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤ ለትምህርት ፍኖተ ካርታው ግብዓት ለማሰባሰብ ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍል ከተውጣጡ 700 ሺህ ሰዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

በተሰበሰበው ግብዓት መሰረትም ትምህርት መጀመሪያ ዕድሜ፣ የአካል ጉደተኞች አካታችነት፣ አገር በቀል እዉቀትና ሙያ ማካተት፣ ስፖርት በትምህርት ቤቶች ዋነኛ ማጠንጠኛ እንዲሆንና የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማካተት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ መቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከልማት ድርጅቶች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት፣ ቴክኒክ ትምህርት፣ ስነ ምግባር፣ የከፍተኛ ትምህት ፕሮግራም የመሳሰሉት ላይ ሰፊ ግብዓት እንደተገኘ አመልክተዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ ተጨባጭ ሁኔታ ካላቸው እንደ ቬትናም ያሉ አገሮችም ተሞክሯቸው እንደተፈተሸና ትምህርት ሊወሰድበት እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከሚኒስቴሮች ከተሰበሰበው ግብዓት ሁሉም ተቋማት ከተቋማቸው ጋር የተሳሰረ እዉቀት ያለዉ ትዉልድ ተፈጥሮ ወደ ስራ አለም ሲመጣ የማይቸገር መሆን እንዳአለበት መገንዘብ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች እና ማህብረሰብ  ክፍሎች ጋር ዉይይት ማድረጉ የተሻለ ፍኖተ-ካርታ ለመቅረጽ ወሳኝ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ጥላዬ በቀጣይ ከ4 ሚኒስቴሮችና በዉጭ  አገር ከሚኖሩ ትዉልድ ኢትዮጵያዊያን ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ውይይቱን በሁለት ወራት ዉስጥ በማጠናቀቅ ፍኖተ ካርታውን በተሰበሰበው ግብዓት መሰረት በማዘጋጀት ወደስራ ለማስገባት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ፍኖተ ካርታው ተጠናቆ ስራ ላይ ሲውል ለ15 አመታት ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም