የሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎች የፓርላማና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ተስማሙ

63
ግንቦት 21/2010 የሊቢያ ተቀናቃኝ ቡድኖች ዛሬ በፓሪስ ባደረጉት ስብሰባ በፈረንጆቹ ታህሳስ 10 ቀን የህዝብ ተወካዮችና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሀገሪቱ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ ያደረጉት መቀመጫቸውን በትሪፖሊ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ፋየዝ ሲራጅ አማካሪ ጣህር አል ሶኒ ናቸው። አማካሪው በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ አራት ፓርቲዎች በፓሪሱ ውይይት የተሳተፉ ሲሆን፥ በመጪው መስከረም 16 ቀን ለምርጫ ምቹ የሆነ ህገመ ንግስታዊ ሂደትን ለማጠናቀቅ መግባባት ላድ ደርሰዋል ነው ያሉት። ሊቢያ በ2011 ሙዓመር ጋዳፊ ከተገረሰሱ ወዲህ በፖለቲከኞች አቋም መለያየት የተሰነጣጠቀች ሲሆን ከ2014 ወዲህ ደግሞ መቀመጫቸውን ትሪፖሊ እና በምስራቅ ባደረጉ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ተቀናቃኞች ውጥረት ላይ ናት። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በነዳጅ ሃብቷ የምትታወቀው እና አሁን ቀውስ ላይ የምትገኘው ሊቢያ እንደገና አንድ ወደመሆን እንድትመጣና ሀገራዊ  ምርጫ እንድታካሂድ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። የፓሪሱ ውይይት በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል መቀመጫውን ያደረገው ቡድን መሪ ኮማንደር ከሊፋ ሃፍጣር እና በትሪፖሊ መቀመጫውን ያደረገው አስተዳደር ጠቅላይ  ሚኒስትር ፋየዝ ሲራጅን ያሳተፈ ነው። የማልታ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆሴፍ ሙስካት የሊቢያ ሁሉም ኃይሎች ያሳዩት ዝግጁነትና ፈቃደኝነት እንዲተገበር ልናግዛቸው ይገባል ነው ያሉት። ሮይተርስ በውይይቱ ወቅት መግባባት ላይየተደረሰበትን ሰነድ ዋቢ አድርጎ እንዳስነበበው  ብሄራዊ የጦር ሰራዊት ለማቋቋም፣ ሀገራዊ ውህደቱን ለማፋጠንና ማዕከላዊ ባንክ ለመመስረት ታቅዷል። አካታች የሆነ ብሄራዊ የፖለቲካ ስብሰባ እንዲካሄድና በምርጫው ውጤት ላይ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ወገኖች ላይ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀብ ለመጣል ያለመ ሀሳብ እንደተካተተበትም ተጠቅሷል። በስብሰባው ላይ በተባበሩት መንግስታድ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አምስት ቋሚ አባል ሀገራት(ፈረንሳይ፣ ቻይና አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ብሪታኒያ) እንዲሁም ጣሊያን፣ ቱርክ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ኳታር እና የሊቢያ አጎራባች ሀገራት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም