ኢትዮጵያና ኢኳዶር ሁለንተናዊ ትብብራቸውን ለማሳደግ ተስማሙ

78
አዲስ አበባ ግንቦት21/9/2010 ኢትዮጵያና ኢኳዶር ሁለንተናዊ ትብብራቸውን ለማሳደግ የሚረዳ የግንኙነት መድረክ ለመፍጠር ተስማሙ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የኢኳዶር አቻቸውን ማሪያ ፌርናንዳን  በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በኢትዮጵያና ኢኳዶር መካከል እስከ አሁን የሁለትዮሽ መደበኛ የፖለቲካ የምክክር መድረክ ሳይመቻች መቆየቱን አስመልክተው መነጋገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም አስታውቀዋል። በመሆኑም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረግ መደበኛ የፖለቲካ የግንኙነት መድረክ ለማመቻቸት መስማማታቸውን ገልጸዋል። ውይይቱ የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትብብር መሰረት ለማሻሻል ዓላማ ያደረገ መሆኑን ነው አቶ መለስ የተናገሩት። የኢኳዶር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በአበባ እርሻ ልማት እየተሳተፉ ሲሆን ዘርፉን በቴክኖሎጂ ልውውጥ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውንም ጠቅሰዋል። እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢኳዶርን ማዕከል አድርጎ ወደ አካባቢው አገራት የበረራ መዳረሻውን ቢያሰፋ ሲሉ ሃሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። ኢኳዶር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2018 እና 2019 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት ለመሆን እንደምትወዳደር መግለጻቸውንና ለዚህም ኢትዮጵያና የአፍሪካ አገራት ድጋፍ እንዲሰጡ ጠይቀዋል ብለዋል። ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ምርጫ ኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምትሰጥና ሌሎችም የአፍሪካ አገራት እንዲደግፉ ጥረት እንደምታደርግ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ዶክተር ወርቅነህ አክለውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የምታካሄደውን ጥረት ለሚኒስትሯ አስረድተዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም