በሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በተለያዩ ግዜያት ቢካሄዱም የተነሱበትን አላማ ስተዋል--- ምሁራን

90

የካቲት 19/2011 በኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በየወቅቱ ቢካሄዱም የተነሱበትን አላማ ከግብ ከማድረስ ይልቅ በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች በመጠለፋቸው ለእርስ በርስ  አለመግባባት መንስኤ መሆናቸውን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ምሁራኑ እንዳሉት ሁሉም ትውልድ ለሀገር ግንባታ የራሱን አሻራ ጥሎ ቢያልፍም፤ ከራሱ ፍላጎት አንጻር ታሪክን መጠቀሙና በውጪ ሀገራት የቀሰሙትን ተሞክሮ በተገቢው መንገድ ወደ ሀገራቸው  ያለማምጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡ 

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የህግና የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ  እንደሚሉት  በሀገሪቱ  ታሪክ የዴሞክራሲም ሆነ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች ከተነሱበት አላማ  ይልቅ ለአሁኑ የፖለቲካ ክፍፍልና አለመረጋጋት መሰረት መሆናቸውን አስረድተዋል ፡፡

በማሳያነትም የመሬት ላራሹ ና የትምህርት ጥራት ጥያቄን፤ ውጭ ተምረው የመጡ ምሁራን የውጪውን ተሞክሮ ከሀገሪቱ ባህል ጋር  ያለመቃኘታቸው ለፖለቲካ ሽኩቻ መንስኤ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በውጭ ሀገር ተምረው የመጡ ምሁራን የኖሩባቸው ሀገራት የሰጥቶ መቀበል፤ የሀሳብ ብዝሀነትና የዴሞክራሲ መርህ ማንጸባረቅ ሲገባቸው እርስ በርስ በመከፋፈል ተመሳሳይ ሀይማኖት ያላቸው እንኳ በብሄር ተቧድነው ማምለካቸውን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡

“ሀገራችን ከሶስት ሺ አመት በላይ  በነጻነት የቆየችው  በጀግኖች አርበኞችና በሁሉም ህዝብ ተሳትፎ ነው”  ያሉት ደግሞ  የጀግኖች አርበኞች ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት አምባሳደር አለማየሁ አበበ ናቸው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም በኑሮዋቸው ቢጎሳቆሉ፤ በመንግስታቸው ቅሬታ ቢኖራቸውም ለነጻነታቸው በአንድነት እንደሚነሱ የገለጹት አምባሳደር አለማየሁ  ይህን ታሪክ የሚሸረሸር እንቅስቃሴና ለፖለቲካ ጥቅም በማዋል የታሪክ ሽሚያ እየተስተዋለ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች  ለመቅረፍም   የአሁኑ ትውልድ  በመነጋገር መፍታት አለበት ነው ያሉት ፡፡

የዴሞክራሲ ባህልን ጠንቅቆ ባለመረዳት፤  በመቻቻል የልዩነት ሃሳብን ከማስተናገድ ይልቅ የኔ ብቻ ይደመጥ አስተሳሰብ እየዳበረ መምጣቱንም ፕሮፌሰር መረራ ይናገራሉ፡፡

ፕሮፌሰር መረራ እንዳሉት “በኛ ዘመን ወጣቶች በተማሪዎች ንቅናቄ ቢሳተፉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን ወስደውታል፤ ከነሱም ቢሆን የወታደሩ መንግስት ቀምቷል፡፡  በኢህአዴግም  ቁጥራቸው የበዛ ወጣቶች ቢሳተፉም ያላቸውን አቅም አልተጠቀሙም”፡፡

ሀገር ሲገነባ  አለመግባባት መከሰቱ  በአለማችን  የተለመደ  ነው  የሚሉት ዶክተር አልማው  በጣሊያን የውህደት እንቅስቃሴ  ጁሴፔ ማዚኒና ጋሪ ባልዲ ከ33 ትንንሽ መንደሮች የአሁኗን ቅርጽ  እንዲትይዝ ማድረጋቸውን ገልቷል፡፡

’’ጀርመን የተዋሄደችው ብለድ ኤንድ አይረን በሚል  ትግል ከ34 ትንንሽ መንደሮች ነው፡፡ አሜሪካንም ሰሜንና ደቡብ ከሚል የእርስ በርስ ሽኩቻ በተመሳሳይ መንገድ ነው የተዋሄደችው ፡፡ ይህን መሆኑ እየታወቀ የኢትዮጵያን የትግል ታሪክ ክስተት የተለየ አድርጎ ለዛሬ የፖለቲካ ፍጆታ ማዋል አያስፈለውግም” ይላሉ ዶክተር አልማው። 

ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው “ወጣቶች  ከነባሮች ልምድ ወስደው ራሳቸውን አልቻሉም።  እስካሁንም የስልሳዎቹ ትውልድ ፖለቲካውን እየመሩት ነው፤ ይሄም የአፍሪካ ዋና ችግር ነው’’ በማለት ይገልጻሉ።

ወጣቶች ለለውጥ ትልቁን አቅም ቢያበረክቱም  አላማው በአንጋፋዎቹ በመጠለፉ ለውጡ ግቡን አልመታም በማለትም ጨምረው ያስረዳሉ።

በሀገሪቱ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በየግዜው ቢደረጉም በየካቲት ወር በርካታ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል ያሉት ዶክተር አልማው እነዚህ እንቅስቃሴዎች ግን አላማቸውን አላሳኩም ብለዋል።   

ሁሉም ትውልድ የራሱ ታሪክና የሀገር ግንባታ አሻራ ቢኖረውም ይህን በእውቀት መዝግቦ የማስቀመጥ  ጉድለት እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡

“ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ በመሆኑ ታሪክን መማሪያ  እንጂ የእርስ በርስ መቆራቆሻ መሆን የለበትም፤ ይልቁን ካለፈው ስህተት በመማር ለመጪው ጊዜ በጋራ የምሰራበት ሊሆን ይገባል” በማለት  ዶክተር መረራ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

የሀገሪቱ  የነጻነት ተጋድሎ እንዳሁኑ የተደራጀ ጦር ሰራዊትና የጦር መሳሪያ በሌለበት በሀገር በቀል መሳሪያ ዳር ድንበር ማስከበር ለቻሉት ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት  አምባሳደር አለማየሁ፤ ህዝብን  በአንድነት በማንቀሳቀስ በዘመኑ የተከፈለውን መስዋዕትነትና  አርአያነትን ማስቀጠል የትውልዱ ኃላፊነት ነው በማለትም  ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም