የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ቬትናም ገቡ

88

የካቲት 19/2011 የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለሚያደርጉት ውይይት ቬትናም ገብተዋል።

ሁለቱ መሪዎች በቬትናም በሚያደርጉት ውይይት ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ መርሃ ግብሯን እንድታቆም ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ኪም ጆንግ ኡን ወደ ቬትናም የተጓዙት በባቡር ሲሆን ዶንግ ዳንግ የተሰኘችው ከተማ ሲደርሱ በቬትናም ባለስልጣናት ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።።

ከባቡር ጣቢያው በከፍተኛ ጥበቃ ታጅበው በመኪና ወደ ሃኖይ ያመሩ ሲሆን ዋና ረዳታቸው እና እህታቸው ኪም ዮ ጆንግ አብሯቸው መጓዟ ተሰምቷል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ወደ ቬትናም ዋና ከተማ ሃኖይ እየተጓዙ መሆኑን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሁለቱ መሪዎች በቬትናም ዛሬ ማታ በሚያደርጉት አጭር የፊት ለፊት ቆይታ የጋራ እራት ፕሮግራም እንደሚኖራቸው ተነግሯል።

መሪዎቹ በድጋሚ በመጪው ሀሙስ ለመገናኘት መርሃ ግብር ተይዞላቸዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ከስምንት ወራት በፊት በሲንጋፖር ተገናኝተው ታሪካዊና የመጀመሪያ ውይይታቸውን አድርገዋል።

በሲንጋፖር በነበራቸው ቆይታ ሁለቱ መሪዎች የኮሪያ ልሳነ ምድርን ከኒዩክሌር መሳሪያ ስጋት ነጻ ለማድረግ መወያየታቸው ይታወቃል።

ምንጭ፦ሮይተርስ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም