የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወደ አገር ለሚገቡና ለሚወጡ ተጓዦች አስገዳጅ የቢጫ ወባ ክትባት እንደሚሰጥ አስታወቀ

64

አዲስ አበባ የካቲት 18/2011 ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡና ለሚወጡ ተጓዦች አስገዳጅ የቢጫ ወባ ክትባት እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለአለም አቀፍ ተጓዦች የቢጫ ወባና ሌሎች ክትባቶች የሚሰጥባቸው ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁሟል።

ለተጓዦች አስገዳጅ የቢጫ ወባ ክትባት ለመስጠት በአራት ከተሞች ላይ የክትባት መስጫ ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጸው ኢንስቲትዩቱ በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያና በመቐለ ለማዕከል ግንባታ የሚሆነውን ቦታ ማግኘቱን ገልጿል።

በኢኒስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤናና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ አብርሃም ሙሉነህ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱ በተለያዩ የግል የጤና ተቋማት ይሰጥ ነበር።

የማዕከላቱ መቋቋም ተጓዞች ክትባት ሲፈልጉ ብቻ ይሰጥ የነበረውን ክትባት ማንኛውም ወደ አገር ውስጥ የሚገባም ሆነ ከአገር የሚወጣ ተጓዥ በግዴታ ክትባቱን እንዲወስድ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት በአራት ዋና ዋና ክልሎች መግቢያዎች በተለይም የአውሮፕላን ማረፊያ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ የቢጫ ወባና ሌሎች ክትባቶች የሚሰጥባቸው ማዕከላትን በአዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ ባህርዳር እና መቀሌ ከተሞች በማስፋፋት አገልግሎት የመስጠት ስራ እንደሚተገበር ተናግረዋል።

ቦታ ከተገኘባቸው አዲስ አበባና መቐለ በተጨማሪ በሐዋሳና በባህር ዳር ከተሞች ሳይቶችን የማስፋፋት ስራ ፈቃድ ከተገኘና መድሓኒት ከተሟላ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን መስጠት እንደሚጀመርም አስታውቀዋል። 

የክትባት አገልግሎት ሰዎች ራሳቸውን ከበሽታ መከላከል እንዲችል በተለያዩ መንገዶች ይሰጣል።

ይህንንም በመከላከል ረገድ በተለይም በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ያሉ አገራት ከፍተኛ ስራ የሚሰሩ ሲሆን በኢትዮጵያም የሌሎቹን አገራት ተሞክሮ በመውሰድ ለህብረተሰቡ ስጋት ይፈጥራሉ የሚባሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ዓለም ዓቀፍ ተጓዦች በተለይም ቆላማ ወደሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚጓዙ እድሜያቸው ከዘጠኝ ወራት የዘለሉ ተጓዦች የቢጫ ወባ ክትባት እንዲወስዱ ይመክራል።

ለሁለት ዓላማዎች የቢጫ ወባ ክትባት እንደሚሰጥ የሚገልጸው የዓለም የጤና ድርጅት የበሽታውን ስርጭት መግታት እንዲሁም ግለሰቦች በጉዞ ላይ እንዳሉ ለበሽታው ተጋልጠው የከፋ የጤና ችግር እንዳያጋጥማቸው ለመከላከል እንደሆነ ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም