ፍርድ ቤቱ በአቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ የተጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ

63

ባህር ዳር የካቲት 18/2011 በቀድሞው የጥረት ኮርፖሬት ከፍተኛ ኃላፊዎች አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ የተጠየቀውን የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ፈቀደ፡፡

የባህር ዳርና አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ዓርብ በዋለው ችሎት የቀረበውን ሰነድ በመመርመር የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለውን ለመወሰን ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የአማራ ክልል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ የዳሽን ቢራ አክሲዮን ማህበር ሽያጭ ህጋዊ መሆንና አለመሆኑን በዘርፉ ባለሙያዎች ለማጣራት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል፡፡

እንዲሁም የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ኦዲት ያልተጠናቀቀ በመሆኑና ወሳኝ የሆኑ በውጭ ለሕክምና የሄዱ ሁለት የሰው ምስክሮችን ቃል ለመቀበል የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጥያቄውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

ችሎቱ በበኩሉ ቀደም ሲል በተሰጠው የ14 ቀን ቀጠሮ አቃቤ ህግ ዘጠኝ የሰው ምስክሮችንና ከ20 በላይ ሰነዶችን አሰባስቦ ጉዳዩን የማጣራት ሥራ ስለማከናወኑ አቃቤ ህግ ያቀረበውን ሰነድ በመመርመር ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

ከጉዳዩ ውስብስብነትና የቀረቡትና ያልተጠናቀቁ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ማለትም የኦዲት፣ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ምስክሮችን ቃል የመቀበልና የአክሲዎን ሽያጩን ህጋዊነት የማረጋገጥ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ችሎቱ አምኗል፡፡

በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮች አጣርቶ ለማቅረብ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቢ ህግ ያቀረበውን የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ጥያቄ በመፍቀድ ችሎቱ ለመጋቢት 2 ቀን 2011 ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ለጉዳያቸው ቀርቦ የሚከራከር ጠበቃ ማግኘት ባለመቻላቸው ከባለሙያ ጋር ለመመካከር በማረሚያ ቤት ውስጥ የስልክ፣ የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ማረሚያ ቤቱ በበኩሉ የስልክና የኮምፒዩተር አገልግሎት በግቢው ውስጥ እንዳለና እንደማንኛውም ታራሚ መጠቀም እንደሚችሉ ለችሎቱ ማስታወቁን  ተመልክቷል፡፡

ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ ለተነሳውም አካባቢው ከከተማ ክልል ውጭ በመሆኑ የኢንተርኔት ግንኙነት እንደሌለና ለግል ተብሎ የሚፈቀድ የኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖሩን ለችሎቱ አሳውቋል፡፡

በመሆኑም ከማረሚያ ቤቱ የቀረበለትን ማስረጃ መሰረት በማድረግ ችሎቱ ሁለቱ ታሳሪዎች የስልክ፣ የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት አግልግሎት ለማግኘት ያቀረቡትን ጥያቄ ባለመቀበል ውድቅ አድርጓል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም