የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል በደብረ ማርቆስና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ተከበረ

67
ደብረ ማርቆስ/ አርባ ምንጭ ሚያዚያ 28/2010 ወጣቱ ትውልድ አንድነቱን በማጠንከር ሃገሩን ከድህነትና ኋላቀርነት በማላቀቅ የአባቶችን ለጠላት አልደፈርም ባይነት ታሪክ ሊደግም  እንደሚገባ ተጠቆመ። 77 ተኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል በደብረ ማርቆስና በአርባ ምንጭ ዮኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ሲስተር ገነት ደጉ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን የአርበኝነት ተጋድሎ ታሪክ በመረዳት የራሱን የጀግንነት ታሪክ ሊሰራ ይገባል። የኢትዮጵያን ነጻነት በደማቸው ያስከበሩ ጀግኖች አርበኞች በታሪክ ውስጥ የሚገባቸውን ቦታና ትኩረት እንዲሰጣቸው በማድረግ በኩል ተተኪው ትውልድ አርአያነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም አስረድተዋል። የአባቶቹን ለጠላት አልደፈርም ባይነት የጀግንነት አርማ ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን ከድህነትና ኋላቀርነት በማላቀቅ ሊደግም እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በመድረኩ ላይ የጎጃም አርበኞች ተጋድሎ ለኢትዮጵያ ነጻነት በሚል ጽህፍ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር ሰለጠነ ስዮም እንዳሉት ትውልዱ ለታሪኩና ለባህሉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። በተለይ ደግሞ የደም እና የአጥንት ዋጋ የተከፈለበትን ነጻነት እንደቀላል ሊታይ እንደማይገባው አስረድተዋል። "ጀግኖች አርበኞች በመረዳደትና  ሕብረት በመፍጠር ጠላትን መመከትና የሀገርን ነጻነት ማስጠበቅ መቻላቸው ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ትምህርትና የቤት ሥራ ነው" ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በበኩላቸው "ወጣቱ የታሪክ አደራውን በአግባቡ ተረድቶ የራሱን ድረሻ በልማትና በሀገር ግንባታ ማሰየት ይኖርበታል" ብለዋል። " ተተኪው ትውልድ የሀገር እና የወገን ፍቅርን በመላበስ አንድነቱን አጠናክሮ ለልማት ዘብ መቆም ይጠበቅብናል" ያለው ደግሞ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የማናጅመንት ተማሪ ታዘበው ጸጋዬ ነው። በተመሳሳይ 77ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትናንት በተላየዩ ዝግጀቶች ተከብሯል። በበዓሉ ላይ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተማሪዎች እንዳሉት፣ በፋሺስት ጣሊያን ላይ አርበኞች የተቀዳጁትን ድል በልማት ሊደገም ይገባል ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን አቶ ሙልጌታ ደበሌ ጀግኖች አባቶች መላው የኢትዮጵያን ህዝብ በአንድነት በማንቀሳቀሳቸው ፋሺስት ጣሊያንን ማሸነፍ እንደቻሉ ተናግረዋል ፡፡ "ይህን በደማቅ ቀለም የተጻፈውን የአባቶቻችን ታሪክ ወጣቱ ትውልድ እንዲያውቀው ብቻ ሳይሆን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በድህት ላይ ድል እንዲቀዳጅ ማድረግ ይገባል" ብለዋል፡፡ "አገራችን ኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነቷን መጠበቅ በመቻሏ ለቅኝ ግዛት እጅ ያልሰጠች አገር ልትሆን ችላለች" ያሉት ደግሞ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና የዕለቱ ክብር እንግዳ ዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማሪያም ናቸው። የኢትዮጵያ አርበኞች ውድ ህይወታውን፣ አካላቸውንና ጥሪታቸውን ሳይሰስቱ የከፈሉት የሀገር ፍቅራቸውን ለመግለጽና ብሔራዊ ራዕይ ለማሳካት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ "ታሪክ የሚዘከረው ለዛሬና ለነገ እንጂ ለትናንትና አይደለም" ያሉት ዶክተሩ አዲሱ፣ ትውልዱ እንደቀደምት አርበኞች ሁሉ ለብሔራዊ ማንነቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊተጋ እንደሚገባ ገልጸዋል ፡፡ በታሪክና ቅርስ አስተዳር ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በለጠ ታምሬ በበኩሉ "የአሁኑ ትውልድ እንደጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች የሕይወት መስዋዕትነት ሳይጠበቅብን የድህነት ታሪክን ለመቀየር ጠንክረን እንሰራለን" ብሏል። ለእዚህም ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማጠናከር ሲቻል በመሆኑ ሁሉም ሰው በተሰማራበት መሰከ እርስ በርስ የመደጋገፍና የመተጋገዝ ባህልን ማዳበር እንዳለበት አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም