በባኮ ከተማ የተገነባው ሆስፒታል ለአገልግሎት በቃ

60

አምቦ የካቲት 18/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ከተማ  74 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

ሆስፒታሉን ትናንት መርቀው ስራ ያስጀመሩት  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝደንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን እንዳሉት የጤና አገልግሎትን በማስፋፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በከፍተኛ ወጪ የተገነባው ሆስፒታሉ ረጅም አገልግሎት እንዲሰጥ  የአካባቢው ህብረተሰብ  ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርግለት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ  በበኩላቸው ሆስፒታሉ በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ፣በሰው ኃይል፣ በሕክምና ቁሳቁስ   በመደራጀት ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል፡፡

ባኮን ጨምሮ ለስምንት አጎራባች ከተሞች ለሚገኙ 750 ሺህ ነዋሪዎች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለውም አመልክተዋል፡፡

የባኮ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ቢቂልቱ ፈይሳ በሰጡት አስተያየት የሆስፒታሉ መገንባት ለረጅም ጊዜ ለነበረው ጥያቄያቸው ምላሽ ማግኘቱን ተናግረዋል።

"የተሻለ ህክምና አገልግሎት ፍለጋ ወደ አምቦና አዲስ አበባ ሲያደርጉት የነበረውን ጉዞ በማስቀረት ከእንግልትና ከወጪም ይታደገናል" ብለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ በቀለ ነጋሳ  በበኩላቸው የሆስፒታሉ መሰራት ችግራቸውን እንደሚያቃልላቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም