''አርሶ አደሩ በተፈጥሮ ሀብት ሥራና አጠባበቅ ላይ እንዲያተኩር ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል''- ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ

59

ደብረብርሃን የካቲት 17/2011 ለአርሶ አደሩ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ማረጋገጫ ዘመናዊ ካርታና ደብተር ከመስጠት ባሻገር በተፈጥሮ ሀብት ሥራና አጠባበቅ እንዲያተኩር ድጋፍ  እንዲደረግለት  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዛሬ  አሳሰቡ።

በአማራ ክልል ለሰሜን ሸዋ ዞን  አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለአርሶ አደሩ ተሰጥቷል።

ሁለተኛ ደረጃ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማለት በዘመናዊ ካርታ የተደገፈ ሆኖ አዋሳኞችን ያሳያል።

አርሶ አደሩ የመሬቱን ካርታ አስይዞ ከገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ገንዘብ በመውሰድ ኑሮውን የሚያሻሽልበት፣ ሊያከራይ፣ ለልጆቹም ሊያወርስበት ይችላል፡፡

የመጀመሪያው የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር አርሶ አደሩ የመሬቱን መጠን ለይቶ የማያውቅበትና ለብድር የማይጠቀምበት ነበር፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብረ ብርሃን  ከተማ ካርታና ደብተሩንለአርሶ አደሮች ሲሰጡ እንዳስገነዘቡት አመራሩ የአርሶ አደሩን በመሬቱ የመጠቀም መብቱን ከማረጋገጥ በላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራውን ማገዝ ይገባዋል።

በዘመናዊ  መንገድ የተካሄደው የመሬት ልኬት በዘርፉ የሚነሱትን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንደሚፈታም እምነታቸውን ገልጸዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብአት አጠቃቀምን ለማሻሻል እንደሚበጅ አቶ ደመቀ አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀጋ አራጌ በክልሉ 70 ወረዳዎች በካርታ የተደገፈ የሁለተኛ ደረጃ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ካርታ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

እስካሁንም በ23ወረዳዎች ለሚኖሩ ሦስት ሚሊዮን አርሶ አደሮች  ካርታና ደብተሩ  መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም መሬታቸውን በአግባቡ ለመንከባከብ እንደሚያስችልና ከአበዳሪ ተቋማት ገንዘብ ወስደው ለመሥራት ያስችላቸዋል ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድም አገኘሁ በዞኑ 264ሺህ አርሶ አደሮች የምስክር ወረቀቱ ተጠቃሚ  መሆናቸውን  አስታውቀዋል።

በመጀመሪያ ደረጃ  ይዞታ  ማረጋገጫ ደብተር  አሰጣጥ ላይ ባጋጠሙ ተግዳሮቶች በተጭበረበረ ማስረጃ መብታቸውን የተነጠቁ ከ93 በላይ ሰዎች  መሬታቸው እንደተመለሰላቸውም ገልጸዋል።

ከእንሳሮ ወረዳ ወቀሎ አንፆኪያ ቀበሌው  አርሶ አደር ፍቅረ ማሪያም ሳህለ ለሁለት ሄክታር መሬት የተዘጋጀውን ደብተርና ካርታ መቀበላቸውንና ይህም በመሬታቸው ተጠቃሚ  እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።

በዚህም ከግብርና ሥራቸው በተጓዳኝ በንግድ ሥራ ለመሳተፍ  ብድር ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

የቀወት ወረዳ አርሶ አደር ጌጤነሽ ጎርፉ በበኩላቸው  ደብተሩና ካርታው የገጠር ሴቶች መሬታቸውን በጉልበተኞች ይነጠቁ የነበረውን ሁኔታ  እንደሚፈታ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም