የኢትዮ ህንድ የኢኖቬሽን፣ ሳይንስና ቴክኖለጂ ፕሮግራም ይፋ ተደረገ

71

አዲስ አበባ የካቲት 17/2011 ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ በመቀጠል የፕሮግራሙ ሁለተኛ ተጠቃሚ አገር የሆነችበት የኢትዮ ህንድ ኢኖቬሽን፣ ሳይንስና ቴክኖለጂ ኮሜርሻላይዜሽን ፕሮግራም ባለፈው አርብ በህንዷ ሃይደራባድ ከተማ ይፋ ተደርጓል።

ስምምነቱ ህንድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ትብብር እንደሚያሳድግም ታምኖበታል።

የህንድ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሃርሻ ቫርዳሃን ከኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ጋር በመሆን ፕሮግራሙን በይፋ አስጀምረዋል።

ፕሮግራሙ ይፋ የተደረገው በህንድ “ቀጣይነት ላለው እድገት በምርምርና ልማት ላይ አለም አቀፍ ትብብር መፍጠር “ በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው 6ኛው አለም አቀፍ የምርምርና ልማት የ2019 ጉባኤ ላይ ነው።

አፍሪካም የመርኃ ግብሩ አጋር አህጉር መሆኗ  የተጠቀሰ ሲሆን ከህንድ የሳይንስና ቴክኖለጂ እድገት ተጠቃሚ እንደምትሆንም ተገልጿል።

በዚሁ ወቅት ሃርሻ ቫርዳሃን ”የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ራዕይ ለአፍሪካና ህንድ የጋራ ብልጽግና ያለንን ቴክኖለጂና ኢኖቬሽን እንድናጋራ ነው'' ብለዋል።

ህንድ በደቡብ ደቡብ ግንኙነት በመታገዝ የሁለትዮሽና የተናጠል ግንኙነት መደላድል በማስቀመጥ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲያስመዘግቡ እገዛ የምታደርግ መሆኗን ገልጸዋል።

ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው ህንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት መቀጠል እንዳለባት ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ እያደገ ከመጣው የህንድ የኢኖቬሽንና የሳይንስና ቴክኖለጂ ትብብርና ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ እንደምትሆን ተስፋ አለኝ” በማለት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት የህንድ የቴክኖለጂና ኢኖቬሽን ሳምንትን በአዲስ አበባ እንደምታዘጋጅ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም