የ70 ዓመታት የትዳር አጋሮች በተመሳሳይ ሰዓት ዓለምን ተሰናበቷት

1259
በአምቦ ከተማ ለ70 ዓመታት በትዳር ተሳስረው የቆዩት አቶ ጉርሜሣ ኢሬንሶ የ101 እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ጉዲሴ ቂጣታ ደግሞ የ85 ዓመት ባለጸጎች በአንድ ቀን በተመሣሣይ ሰዓት ዐርፈዋል።

አምቦ የካቲት 17/2011 በአምቦ ከተማ ለ70 ዓመታት በትዳር ተሳስረው የቆዩት አጋሮች በአንድ ቀን በተመሣሣይ ሰዓት ዐርፈዋል፡፡

የአቶ ጉርሜሣ ኢሬንሶና ወይዘሮ ጉዲሴ ቂጣታ በአምቦ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪዎች ነበሩ ፤ ለሰባት አሥርት ዓመታት የዘለቀው ትዳራቸው ባለፈው ዓርብ እስኪያበቃ ድረስ፡፡   

በዚህ በረጅም የትዳር ቆይታቸው 18 ልጆችን አፍርተዋል፤ በርካታ የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡  

አቶ ጉርሜሣ ኢሬንሶ የ101 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ነበሩ።

ባለቤታቸው ወይዘሮ ጉዲሴ ቂጣታ ደግሞ በዚህች ምድር የኖሩት ለ85 ዓመታት ነበር፡፡ 

ባልና ሚስቱ በትዳር ያሳለፏቸው ዘመናት ፍቅር የተሞላባቸው እንደነበሩ ወዳጆቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ይናገራሉ፡፡  

እነኚህ የዕድሜ ባለጸጋ ባልና ሚስት በእርጅና ምክንያት አልጋ  ላይ ከዋሉ ጥቂት ወራት እንዳስቆጠሩ የቤተሰቡ አባል አቶ በፍቃዱ ማዴሳ ለኢ ዜ አ ሪፖርተር ገልጸውለታል፡፡

የትዳር አጋሮቹ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት በተመሳሳይ ሰዓት እኩለ ሌሊት ላይ ይህቺን ዓለም ተሰናብተዋል፡፡ 

አቶ ጉርሜሳ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲያርፉ፣ከግማሽ ሰዓት በኋላ ደግሞ በሌላው የመኖሪያ ክፍል አልጋ ይዘው የነበሩት ባለቤታቸው ተከትለዋቸዋል።

የባልና ሚስቱ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ትናንት በአምቦ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ 

እውነተኛው ፍቅር እስከ መቃብር ይሄ ይመስላል።