የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ህገ መንግስቱን መሠረት ያደረገ ምላሽ ሲሰጥ አልነበረም- ምሁራን

82

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 በኢትዮጵያ ከማንነትና ከወሰን ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ግጭቶች ህገ መንግስቱን መሠረት ያደረገ ምላሽ ሲሰጥ እንዳልነበር የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

ለህዝቡ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በህገ መንግስቱ ያልተካተቱ ጉዳዮችን በማካተት ማሻሻል አማራጭ የሌላው መፍትሄ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የጸደቀበት ሂደትና ይዘቱ ላይ የተለያዩ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በድጋሚ ውይይት ተደርጎበት ሊሻሻል እንደሚገባም አመልክተዋል።

መንግስት የአገሪቷን ህዝቦች በበቂ ሁኔታ ሳያወያይ በ1986 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የህገ መንግስት አርቃቂ ጉባዔ ማቋቋሙና በህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ህገ መንግስቱ መጽደቁ ተገቢ እንዳልነበረም አስረድተዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የህግና ፌዴራሊዝም ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ጥጋቡ  ''የረቀቀበት የጸደቀበት ሂደት እንዳለ ሆኖ ይዘቱም ላይ ችግር አለ።” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የህገ መንግስት ተመራማሪው አቶ አማን ዑመር በበኩላቸው

''የዛሬ 20 ዓመት ህገ-መንግስቱ ረቋል። የዛሬ 20 ዓመት የኢትዮጵያውያን የኑሮ ደረጃና የዕውቀት ሽግግር የሰው ብዛት የዘመኑ ቴክኖሎጂ የት እንደደረሰ አስበን ህገ-መንግስቱን ያረቀቁት ዜጎቻችን በሰዓቱ ምን አይነት አስተሳሰብ ነበራቸው አሁን ያለነው ዜጎች ምን አይነት አስተሳሰብ አለን። “

አለ የሚለውን ጉዳይ ከግንዛቤ በማስገባት  በአሁኑ ሰአት ህዝብ በማወያየት ማሻሻል ይገባል ብለዋል፡፡

ህገ መንግስቱ የብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ መብት የሰጠ ቢሆንም በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው ብሄርን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ ስርዓት ከማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ፈተናዎችን እያስተናገደ መሆኑን ገልጸዋል።

በፌዴራል ስርዓቱ የዜጎችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች እንዲሁም የአስተዳደር ምቾት ግምት ውስጥ አለመግባቱ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች የግጭት መንስዔ እንዲሆን ማድረጉን  ምሁራኑ አስረድተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር፣ ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 20 ላይ የራስን ዕድል በራስ ከመወስን ጋር የተያያዘ የማንነት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት በክልሉ ያሉ መፍትሔዎችን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ያስቀምጣል።

ይሁንና በተለያዩ አካባቢዎች ከማንነትና ከወሰን ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በክልል ምክር ቤቶች በጊዜ ባለመፈታታቸው ችግሩ ሊባባስ መቻሉን የምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ገብሩ ገብረስላሴ ያስረዳሉ።

በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/5/ መሠረት የብሔር ብሄረሰብ   ዕውቅና ለማግኘት መሟላት ያለባቸውን አምስት መስፈርቶች አስቀምጧል።

እነዚህ መስፈርቶች ቋንቋ፣ ባህል፣ የጋራ ህልውና፣ የሥነ ልቦና አንድነት እንዲሁም የተያያዘ መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር ናቸው፡፡

ይሁንና እስካሁን ባለው ሂደት የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ህገ መንግስታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ውሳኔ እየተሰጠባቸው በመምጣታቸው የግጭት መንስዔ መሆናቸውን ባለሙያዎቹ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የደረሰችበትን የእድገት ደረጃና የህዝቡ ንቃተ ህሊና ታሳቢ በማድረግ ህገ መንግስቱን ማሻሻል እንደሚገባም አመልክተዋል።

መንግስት ከማንነትና ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን አቋቁሞ እየሰራ ነው። 

ኮሚሽኑ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መመዘኛዎችንና ህገ መንግስቱ የተቀበለውን የፌዴራል አስተሳሰብ መሰረት በማድረግ የወረዳ፣ የዞንና የክልል ራስን የማስተዳደር፣ የማንነቴ ይታወቅልኝ፣ የወሰን የማንነታችን ይከበርልን ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ ጉዳዮችን ይመረምራል።

አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከአስተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና ከማንነት ጋር የተያያዙ ግጭቶችና መንስዔዎችን በመተንተን የመፍትሄ ሀሳቦችን ለህዝብ፣ ለፌዴሬሽን እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችና ለአስፈጻሚ አካል ማቅረብን ዓላማው አድርጎም ይሰራል።

ከአስተዳደራዊ ወሰኖች አከላለል፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና ከማንነት ጥያቄ ጋር የተገናኙ ማናቸውንም ችግሮችና ግጭቶችን በጥናት በመለየት አማራጭ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሪፖርት ማቅረብም የተሰጠው ስልጣንና ተግባር ነው።

በህዝቦች እኩልነትና ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር ለማድረግ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክረ ሀሳቦችን ማቅረብ ሌላው የኮሚሽኑ ስልጣንና ተግባር ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም