የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ስኬቱን በወለድ ትርፍ ከመለካት ይልቅ አሰራሩን እዲፈትሽ ተጠየቀ

103

ባህርዳር የካቲት 16/2011 የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም/አብቁተ/የተቋቋመበትን አለማ በመዘንጋት ስኬቱን ከወለድ በሚያገኘው ትርፍ ከመለካት ይልቅ አሰራሩን እንዲፈትሽ ተጠየቀ።

ተቋሙ በበኩሉ በህዝብ ገንዘብ ተቋቁሞ ህዝብን የሚጎዳ ምንም አይነት አሰራር ሊከተል እንደማይችል አስታውቋል።

በክልሉ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ጸሃፊዎች፣ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች የተሳተፉበት የውይይት ማድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

አክቲቪስት መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ተቋሙ የክልሉን ህዝብ ህይወት ለማሻሻል አላማ ይዞ የተቋቋመ ቢሆንም እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው።

ተቋሙ ከማበደሩ ውጭ ተበዳሪው በምን ላይ ቢያውለው ውጤታማ እንደሚሆን የክትትልና የማማከር ስራ እንደማይሰራ ገልጸው የህዝቡን ኑሮ ከማሻሻል ይልቅ ማደህየት እስኪመስል ድረስ በአማካኝ የወለድ መጠን እስከ 16 በመቶ በማስከፈል ደሃውን እየበዘበዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በብድሩ ከመለወጥ ይልቅ ጥሪቱን እንዲያጣ የሚደረግበት ሁኔታ ሰፊ እንደሆነም አብራርተው እንደ ህዝብ ሃብትነቱ ተበዳሪው በተለያየ ምክንያት ብድሩን መክፈል የማይችልበት አጋጣሚ ሲፈጠር የእዳ ስረዛ ማዕቀፍ ሊኖረው ይገባ እንደነበረም ጠቁመዋል።

የአማራን ህዝብ ስም ይዞ እንደመቋቋሙ አሰራሩ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ መሆን ሲገባው ብድሩን መመለስ ላልቻለ ግለሰብ ሌሎች አማራጮችን ከመጠቀም ይልቅ ቤቱን እስከማስሸጥ የደረሰ በደል እንደሚፈጽምም ተናግረዋል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው “ተቋሙ ለአማራ ክልል ህዝብ ኑሮ መሻሻል ታቅዶ የተቋቋመ እንደመሆኑ ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም” ብለዋል።

ስለክልሉ በመቆርቆር ያገባኛል በሚል የተቋሙን አሰራር ለማሻሻልና የብድር ወለድ መጠኑ መቀነስ እንዳለበት በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚጻፈው ነገር ተቋሙን እውነተኛ የህዝብ ሃብት ለማድረግ ከማሰብ የመነጨ በመሆኑ የተቋሙ አመራሮች በበጎ እንዲወስዱት ጠይቀዋል።

“ተቋሙ ብድር መስጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በጥናት ቢረጋገጥ ህይወታቸው ከተለወጡ ተበዳሪዎች ይልቅ ብድር መክፈል ባለመቻላቸው ምክንያት ያላቸው አንጡራ ሃብት ስለተወሰደባቸው ለስደት የተዳረጉት የክልሉ ተወላጆች ይበልጣሉ”ብለዋል።

ሌሎች በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ መሰል የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ተበዳሪዎቻቸው የተበደሩትን መመለስ የማያስችል አሳማኝ ማስረጃ ሲቀርብ በድር የመሰረዝ የህግ ማዕቀፍ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

“አብቁተ ግን ከማበደር ባለፈ በምን ላይ ባበድራቸው ውጤታማ ይሆናሉ ሳይል የአንድ በሬ ባለቤት ቢሆንም ያንኑ አንድ በሬና ቤቱን ሳይቀር በመሸጥ የመመለስ ህግ በመከተል የክልሉን ህዝብ ወደ ባሰ ድህነት እየከተተው ያለ ተቋም ነው”ብለዋል።

በተጨማሪም ተቋሙ እስከ አሁን ለምን ያክል የክልሉ ህዝብ ብድር እንደሰጠና የምን ያክሉ ህይወት እንደተሻሻለ በጥናት የተደገፈ መረጃ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የተቋሙ ዋና ስራ አስመጻሚ አቶ መኮንን የለውም ወሰን በበኩላቸው የተቋሙ የብድር ወለድ መጠን  ከመንግስት ባንኮች ውጪ በአገሪቱ ካሉ መሰል የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

“ለህዝብ ሲባል ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ተቋቁሞ ህዝብን የሚጎዳ ምንም አይነት አሰራር ሊከተል አይችልም” ያሉት አቶ መኮንን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ጸሃፊዎች የሚጽፉትን ነገር በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ሊሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።

እየሆነ ያለው ህዝቡን የሚጠቅም ስራ ሳይሆን ተቋማትን የማዳከም ስራ ስለሆነ  ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስበው ማንኛውም ክልሉን እወክላለሁ የሚል ፓርቲ በምርጫ ቢያሸንፍ የሚረከበው ይህንኑ የህዝብ ተቋም ስለሆነ ነገሮችን በብስለት መመልከት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

“ተቋሙን በደፈናው መውቀስ ሳይሆን መወቀስ ካለባቸው የተቋሙ አመራሮች ስለሆኑ ተጨባጭ መረጃ ካለም መጠየቅ ይቻላል” ብለዋል።

ተቋሙ የምን ያህል ሰዎችን ህይወት ለውጧል የሚለውን ለማወቅ አለም አቀፍ “ኢምፓክት ሪሰርች”የተሰኘ አጥኚ ተቋምና የክልሉ ገለልተኛ ምሁራን የሚሳተፉበት ጥናት ለማስጠናት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

ከ20 ዓመታት በፊት በአክሲዮን ደረጃ የተቋቋመው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) በአሁኑ ሰአት ከስድስት ሚሊዮን በላይ የቁጠባ ደንበኞችና ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የብድር ደንበኞች እንዳሉት ከተቋሙ የተገኘ መረጃ ያስረዳል።

በውይይቱ ላይ በክልሉ ያገባኛል ብለው ለለውጥ እየታገሉ የሚገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ፀሐፊዎች፣ የተቋማት ሃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም