አካዳሚው ያሰለጠናቸው 600 አመራሮች ተመረቁ

70

መቀሌ የካቲት 16/2011 መቀሌ የሚገኘው የመለስ ዜናዊ ስራ አመራር አካዳሚ ያሰለጠናቸውን 600 አመራሮች ዛሬ ተመረቁ።

ለ47 ቀናት የተሰጠው ስልጠናው ለመካከለኛ አመራሮች መሆኑን የአካዳሚው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጎይቶም ተክለማሪያም ገልጸዋል፡፡

ለአመራሮቹ የህወሓትና  የትግራይ ህዝብ ታሪክ ፣ የሀገሪቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ ጨምሮ በ15 ርዕሶች ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

በምረቃው ስነስርዓት ወቅት የተገኙት የአካዳሚው ዳይሬክተር አቶ ጎበዛይ ወልደአረጋይ ተመራቂዎች ህዝብና ሀገር ማዕከል ያደረጉ ስራዎች በማከናወን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ከተመራቂዎች መካከል አቶ ታደሰ ሃይሉ እና ወይዘሪት ሂሩት ዮሴፍ በህዝብና መንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አካዳሚው ቀደም ሲልም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ ከ2ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የአመራርነት ስልጠና መሰጠቱ ተወስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም