የመስሪያ ቦታቸው የፈረሰባቸው ወጣቶች ለኪሳራ መዳረጋቸውን ገለጹ

86

አዲስ አበባ  የካቲት 16/2011 በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶች ለመስሪያ ተብለው የተሰጡ ቦታዎች "ህገ ወጥ ግንባታ ነው" በሚል እንዲፈርስ መደረጉ ለኪሳራ እንዳደረጋቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ገለጹ።

ወጣት ማሪያማዊት ተስፋዬ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ነዋሪ ናት።

ወጣቷ ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት ሥራ ያልነበራት ሲሆን አረብ አገር ሄዳ ለመስራት በሂደት ላይ እያለች መንግስት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ማመቻቸቱን በአሁኑ ወቅት አብረዋት ከተደራጁት ወጣቶች ትሰማለች።

የወረዳው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ፅህፈት ቤት ሥራ አጥ ወጣቶችን ቤት በመዘገበበት ወቅት እሷም ተመዝግባ የመስሪያ ቦታ በጊዜያዊነት እንደተላለፈላት ትገልፃለች።

ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ. ም ከተረከበች በኋላም ከአዲስ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድር ወስዳ በእንጨት እና በቆርቆሮ በሰራችው ሱቅ ለሁለት ወራት የጀበና ቡና አፍልታ ስትሸጥ ቆይታለች። 

ከቆይታ በኋላ "ህገ ወጥ ናችሁ" በሚል እንዲፈርስ መደረጉን ትገልጻለች።

የመስሪያ ቦታው "ህገ ወጥ ነው" በሚል እንዲፈርስ መደረጉ የወሰደችውን ብድር መክፈል እንደማትችልና ለኪሳራ እንዳጋለጣት እንዲሁም የሞራል ውድቀት እንደደረሰባት ተናግራለች። 

እንደ ወጣት ማሪያማዊት ሁሉ "ሰርተን እንለወጣለን" የሚል ህልም ሰነቀው እንደነበር የሚገልጹት ወጣት ወይንሸት ጌታቸው እና ወጣት ቅድስት ጡሚሶ ተመልሰው ሥራ አጥ ከመሆን ባሻገር የሞራል ውድቀት እና ለዕዳ መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አስተዳደር ለቅሬታ አቅራቢዎቹ ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ. ም ለመስሪያ ቦታ የሚሆን 3 ካሬ መሬት በወር 180 ብር ኪራይ ለሁለት ዓመት ውል መዋዋላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ መኖሩን ኢዜአ አረጋግጧል። 

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርነው የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አስተዳደር ጽህፈት ቤት እንዳለው በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶች ጊዜያዊ የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸውም ሆነ እንዲነጠቁ ትዕዛዝ ያስተላለፈው ክፍለ ከተማው ነው።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አበባ እሸቴ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምላሽ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የተመረጡ ቦታዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶች ተላልፈው እንዲሰጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም የተሰጡ ቦታዎች የእግረኛ መንገድን የሚዘጉ፣ ለከተማዋ አሉታዊ ገጽታ የሚያጎናጽፉ እና አንዳንዶችም ህገ ወጥ ግንባታ በመገንባታቸው እንዲፈርሱ መታዘዙን ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ አበባ ገለፃ ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂው የወረዳ አስተዳደሩ ነው።

እንዲህ ዓይነት ችግር እንዲፈጠር ባደረጉ አመራሮች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የገለጹት ወይዘሮ አበባ በወጣቶቹ ላይ በደረሰው ኪሳራ በመንግስት በኩል የተያዘ በጀት ባለመኖሩ ምንም አይነት የካሳ ክፍያ እንደሌለም ተናግዋል።

ወጣቶቹ በዘላቂነት የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በአስተዳደሩ በኩል እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን "ህገ ወጥ ግንባታ ነው" ተብሎ የመስሪያ ቦታቸው የፈረሰባቸው ወጣቶች ምንም ዓይነት ወጪ ሳያወጡ በቅድሚያ የሥራ ዕድል እንደሚመቻችላቸውም አረጋግጠዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም