በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም ምሩቃን መትጋት አለባቸው …ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን

697

ድሬዳዋ የካቲት 16/2011 የገጠሩን ሕብረተሰብ ጤና በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም ምሩቃን ተግተው መስራት እንዳለባቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አሳሰቡ። 

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና ሙያና በኪነ ሕንጻ ትምህርቶች በመጀመሪያ ዲግሪ ያስተማራቸውን 53 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኪነ ሕንጻ በመደበኛ የትምህርት መርሃግብር ለ5 ዓመታት አስተምሮ ካስመረቃቸው 36 የኪነ ሕንጻ ተማሪዎች መካከል 12ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

ከኪነ ሕንጻ ተመራቂዎች በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ለ3ተኛ ጊዜ በሕክምና ዘርፍ ያስተማራቸውን 17 ተማሪዎችንም በሕክምና ዶክተር አስመርቋል፡፡

በምርቃው ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎቹ ዲግሪና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የተዘጋጀውን ልዩ ሽልማትና ዋንጫ የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ናቸው፡፡

ከንቲባው ባስተላፉት መልዕክት እንዳሉት ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥና በቁርጠኝነት በመስራት በሀገሪቱ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ ተግተው ሊሰሩ ይገባል፡፡

በተለይ ተመራቂ ኃኪሞች የገጠሩን ህብረተሰብ ጤና በአስተማማኝ መንገድ በመጠበቅ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ ታች ህብረተሰቡ ድረስ ወርደው መስራት እንደለባቸው አሳስበዋል፡፡

‹‹የኪነ-ህንፃ ተመራቂዎች የሀገራችን ቀደም የኪነ-ህንጻ ጥበብን ከዘመናዊው ጥበብና እውቀት ጋር በማዋሃድ በሀገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን የዘርፉን ዕድገት ማስቀጠል አለባቸው ›› ብለዋል፡፡

ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለለፉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በበኩላቸው ሁለቱም ሙያዎች ለሀገሪቱ የእድገት ጉዞ መሳካትና ለማህበረሰቡ መለወጥ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የህክምና ባለሙያዎች ሰብአዊ ርህራሄና ታታሪነትን ተላብሰው በህክምና ዘርፍ ልዩ አሻራ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ጠቁመዋል ፤ ‹‹የህክምና ባለሙያዎች በቸልተኝነት ሳቢያ የታመሙ ሰዎች በእጃቸው እንዳይጠፉ ምንግዜም ተጠንቀቁ በማለት›› አሳስበዋል፡፡

“የኪነ ህንጻ ተመራቂዎች በሀገሪቱ ዕድገት ላይ ትልቅ ሚና መጫወት ይገባቸዋል” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዘርአይ መስፍን በበኩላቸው በምረቃው ላይ ተገኝተው በከፍተኛ ማዕረግ ለተመረቁት ተማሪዎች ሽልማት ሰጥተዋል፡፡

የኪነ ህንጻ ተመራቂዎች እስከ መጨረሻ በመማርና እውቀትን በማካፈል ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ግዳጅና ብሩህ ተስፋ ለማሳካት ትኩረት ሰጥትው መንቀሳቀስ እንደለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከተመራቂ ኃኪሞች መካከል 3 ነጥብ 8 ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ዶክተር አቤል ወልደጊዮርጊስ በየትኛውም የሀገሪቱ የገጠር ዳርቻ በመጓዝ ወገኖቹን ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

“ይህም በህክምናው መስክ የተቸገሩትን ወገኖችን የመርዳት የልጅነት ህልሜ እውን ለማድረግ ያግዘኛል” ብሏል፡፡

በኪነ ህንጻ ዘርፍ 3 ነጥብ 5 ውጤት በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ወጣት ትርሲት ታምራት በሀገሪቱ እየጎለበተ ባለው የኪነ-ህንፃ ዘርፍ ሙያዊ እውቀቷን በመጠቀም አንዳች አሻራ ለማስቀመጥ መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን የ3ተኛ ዙር ተመራቂዎች ጨምሮ በሕክምናው ዘርፍ 96 ኃኪሞችን ያስመረቀ ሲሆን በኪነ ሕንጻው ዘርፍም ለ4