ስም የማጥፋት ዘመቻዎች ለአገር የሚጠቅም ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች አንዲደበቁ አድርጓል-አብርሃ ደስታ

60

አዲስ አበባ  የካቲት 16/2011በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ስም የማጥፋት ዘመቻዎች ለአገር የሚጠቅም ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች አንዲደበቁ ማድረጉን የአረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ተናገሩ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ማህበራዊ ሚዲያን ለህዝበኝነት ከመጠቀም እንዲቆጠቡም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ አብርሃ ደስታ ይሀን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለኢትዮጵያ እንምከር በሚል አጀንዳ ዛሬ ባካሄዱት ውይይት ላይ ነው።

እንደ አቶ አብረሃ አገላለጽ፤ "የህዝብ መገናኛ ብዙሃን የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ማስፈጸሚያ" በመሆናቸው በርካታው የህብረተሰብ ክፍል ማህበራዊ ሚዲያን አንደ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ አድርጎ እየተጠቀመ ነው።

ይህም አሁን ካለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ በርካቶች ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ተጽዕኖ ፈጣሪ የመሆን ፍላጎት እንዲያሳዩ ማድረጉን ነው የገለጹት።

ይህ ዓላማውን የሳተ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የመንጋ  አስተሳሰብና  እንቅስቃሴን መፍጠሩንም ተናግረዋል።

የመንጋ አንቅሰቃሴው የፈጠረው  መርን   የለቀቀ ስም የማጥፋት ዘመቻ ደግሞ የተሻለ ሃሳብ ያለቸው ግለሰቦች እንደዲበቁ ማድረጉን ገልጸው፤ ከዚህ አንጻር ማህበራዊ ሚዲያው በጊዜ ሂደት የመናገር ነጻነትን የሚያፍን መሳሪያ ሆኗልም ብለዋል።

ከግለሰቦች በተጨማሪ አንደ ፍርደቤት ያሉ ነጻ ተቋማትም በማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ስር እንዳይወድቁ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ህዝበኝነት ለህዝብና ለአገር ሰለማይጠቅም በተለይ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጤናማ ያልሆነ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴን ሊጋፈጡ ይገባል ብለዋል።

የህዝብ ሚዲያዎች የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ ሳይሆኑ ሁሉንም የህዝብ አካላት እኩል የሚያስተናግዱ ሜዳዎች መሆን አንዳለባቸውም አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም