የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ሊሰሩ ይገባል

94

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 የፖለቲካ ፓርቲዎች ስርዓተ መንግስትና አገርን በመለየት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።

ፓርቲዎቹ ጠባብ ከሆነ ምህዳር ወጥተው ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ለመያዝ መስራት እንዳለባቸውም ተነግሯል።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ "ስለ ኢትዮጵያ እንምከር" በሚል አጀንዳ ውይይት አካሄደዋል።

ትኩረታቸውን በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ ያደረጉ ጽሁፎች ቀርበውም ምክክር ተደርጎባቸዋል።

'አገረ መንግስትና ብሄረ መንግስት በኢትዮጵያ' በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ብናልፍ አንዷለም እንዳሉት፤ አገርንና መንግስትን ቀላቅሎ ማየት በተፎካካሪና ገዥ ፓርቲዎች ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው።

መንግስታትም ተቃውሞ ሲደርስበት አገር ለማፍረስ የተቃጣ ተግባር አድርጎ አፈና የመፈጸምን ተግባር እንደሚያዘወትር ጠቁመው ይህም በኢትዮጵያ አገረ መንግስት ግንባታ ላይ ትልቅ ችግር መፍጠሩን አብራርተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን በመገንዘብ አገር የመገንባት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

ፓርቲዎቹ ህዝብን ከሚለያይ አጀንዳ ወጥተው ፖለቲካዊ ትርክታቸውን በጋራ በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ ማድረግ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል። 

ዶክተር ዲማ ነጋዎ "በአገር ግንባታ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና" በሚል ርዕስ ባቀረቡት የመወያያ ሃሳብ "በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረት ጅማሮ አንድም በሚስጥር ሌላም በትጥቅ ትግል መሆኑ ፓርቲዎቹ ውስንነቶች እንዲኖርባቸው አድርጓል" ብለዋል።

የአሰራር ግልጸኝነት አለመኖርና ለህዝብ ክፍት የሆነ አጀንዳ አለመያዝ ደግሞ በፓርቲዎቹ በስፋት የሚታይ ውስንነት መሆኑን አንስተዋል።

ፓለቲካ ፓርቲዎች ህዝብን ለተመሳሳይ ፕሮግራም የማንቀሳቀስ አቅም ማካበት እንዳለባቸውና ይህን ለማድረግም ህዝብ ላይ የተመሰረተ ሰፊ መሰረት ሊኖራቸው እንሚገባ ተናግረዋል።

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በፖለቲካ ሊሂቃን ሃሳቦች የመጠለፉ ዝንባሌ እየተበራከተ መጥቷል ያሉት ደግሞ "የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ" በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው።

በተማሪዎች ዘንድ ክፍፍል መኖሩና የጥልቅ አሳቢነትና ጠያቂነት ክህሎት መጥፋቱ ደግሞ ለተጠቀሰው ችግር ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ተማሪዎቹ በአገራዊ አጀንዳ ላይ በአንድነት እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።

በተማሪዎች ዘንድ አንድነትና መተባባር እንዲፈጠር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም