ሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር መጋቢት አንድ ይጀመራል

72

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር መርሃ ግብር መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል።

የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ነገ በጅማ ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋር ከፋሲል ከተማ እንዲሁም የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከጅማ አባጅፋር ከሚያደርጓቸው ተስተካካይ ጨዋታዎች በኋላ ይጠናቀቃል።

የሁለተኛ ዙር የሊጉ መርሃ ግብር መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

በዚሁ መሰረት መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ባህርዳር ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሀዋሳ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ ከስሑል ሽረ፣ መከላከያ ከደቡብ ፖሊስና ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ።

መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ጅማ አባ ጅፋር ከአዳማ ከተማ፣ ደደቢት ከመቐለ ሰብዓ እንደርታና ፋሲል ከተማ ከሲዳማ ቡና የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ32 ነጥብ ሲመራ፣ ሲዳማ ቡና በ30 ነጥብ 2ኛ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26 ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ11 ግቦች ሲመራ፣ የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 10 ግቦች ይከተላሉ።

በሌላ በኩል ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም የተጀመረው የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጥሎ ማለፍ ውድድር ከመጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በሚካሄዱ ጨዋታዎች እንደሚቀጥል ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከስሑል ሽረ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሌሎች ቀሪ የጥሎ ማለፉ ጨዋታዎች ቀንና ቦታ ወደፊት ይገለጻል ብሏል ፌዴሬሽኑ።

የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊው ክለብ በ2012 ዓ.ም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በመወከል ይሳተፋል።

መከላከያ የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም