በጋምቤላ ክልል ተከስቶ የነበረውን የኩፍኝ በሽታ መከላከል እንደተቻለ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ

723

ጋምቤላ  የካቲት 16/2011 በጋምቤላ ክልል በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ የነበረውን የኩፍኝ በሽታ ለማጥፋት በተደረገው የክትባት ዘመቻ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል መቻሉን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የበሽታውን ስጋት ከክልሉ ለማጥፋት ክትባቱ በመደበኛ የክትባት መርሃ ግብር ተካቶ ለሁለተኛ ጊዜ እየተሰጠ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማበልጸግ የክትባት ኦፊሰር አቶ ወንድማገኝ ሽፈራው እንዳሉት በሽታው በክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደጋጋሚ ተከስቶ በህጻናት ላይ እስከሞት ድረስ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል፡፡

የኩፍኝ በሽታ በክልሉ ለሚከሰተው የህጻናት ሞት አንድ መንስኤ መሆኑን ጠቁመው በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትኩረት ተደርጎ በመሰራቱ በአሁኑ ወቅት በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች በሽታውን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የኩፍኝ ሽታውን ከክልሉ በዘላቂነት ለማጥፋትና የህጻናትን የመከላከል አቅም ከፍ ለማድረግ የኩፍኝ ክትባት በመደበኛ የክትባት መርሃ ግብር ተካቶ እንዲሰጥ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡

መከላከያ ክትባቱ በመደበኛነት መሰጠቱ ህጻናት በሽታውን የመከላከል አቅማቸው ከዚህ በፊት ከነበረበት 85 ከመቶው ወደ 95 ከመቶና ከዛ በላይ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን በአቅራቢያቸው ባለ የክትባት መስጫ ጣቢያ ወስደው በማስከተብ በሽታውን ለማጠፋት የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ክትባቱ በክልሉ 13ት ወረዳዎች በሚገኙ 32 ጤና ጣቢያዎች በቋሚነትና በተንቀሳቃሽ መርሃ ግብር እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

ልጆቻቸውን ለማስከተብ የመጡ እናቶች ለኢዘኤ እንዳሉት በሽታው በህጻናት ላይ ችግር እንደሚያደርስ ባገኙት ግንዛቤ መሰረት ልጆቻቸውን ለማስከተብ ክትባት ወደሚሰጥበት ቦታ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ልጃቸውን ሲያስከትቡ ከነበሩ ከእነዚህ እናቶች መካከል ወይዘሮ መሰረት ጃለታ በሰጡት አስተያየት ልጃቸውን ከኩፍኝ በሽታ ለመከላከል ሲሉ ወደክትባት ቦታ መምጣታቸውን ተናግረዋል። 

“በተለይም በሽታው በህጻናት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎችና በሌሎችም ትምህርት ማግኘቴ ልጄን ከመጀመሪያው ጀምሬ ተከታትዬ ለማስከተብ አስችሎኛል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

” የኩፍኝ በሽታ ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጥ ባገኘሁት መረጃ መሰረት ልጄን ለማስከተብ ወደ ጤና ጣቢያ መጥቻለሁ ” ያሉት ደግሞ ሌላዋ እናት ወይዘሮ ኛለም ጋርኮት ናቸው፡፡