የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ለ10 ዓመት በመጓተቱ ለችግር መዳረጋቸውን የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

54

ነገሌ የካቲት 16/2011 የገናሌ ነገሌ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ አስር ዓመታት በመጓተቱ ለችግር ተዳርገናል ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ።

የተጠያቂነት አሰራር በመዘርጋቱ የፕሮጀክቱ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ዲዛይና ቁጥጥር ድርጅት አስታውቋል፡፡

በነገሌ ከተማ ቀበሌ 01 ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ ግዛቸው ካሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት የፕሮጀክቱ ግንባታ በ2001 ዓ.ም  ሲጀመር የአካባቢውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ይፈታል በሚል ነዋሪው ተደስቶ ነበር ።

"ግንባታው ለአስር ዓመት በመጓተቱ የነበረን ተስፋ ተሟጧል" ያሉት አቶ ግዛቸው በበጋ ወቅት ነዋሪው የውሃ እጥረት ስለሚያጋጥመው በአህያ ተጭኖ ለሚመጣ የወንዝ ውሃ ለአንድ ባለ 20 ሊትር ጀሪካን 10 ብር  ለመክፈል መገደዳቸውን ተናግረዋል።

የከተማው ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ ሀጂ አብዲ ሮባ በበኩላቸው በአንድ ወቅት የፕሮጀክቱን ግንባታ ለመጎብኘት አድል አግኝተው አንደነበር አስታውሰዋል።

" በወቅቱ ፕሮጀክቱ የዲዛይን ችግር አለበት በሚል የተለያዩ አካላት አንዳቸው በሌላቸው ላይ ክስ ሲያቀርቡ ነበር " ብለዋል።

"የውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጀመር በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የተሰጠን ተስፋ እውን ሳይሆን 10 ዓመት በመሆኑ የሚመለከተው አካል ለችግራችን መፍትሄ ይስጠን" ሲሉም ጠይቀዋል።

በኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ድርጅት ዲዛይና ቁጥጥር የገናሌ ነገሌ ፕሮጀክት አማካሪ ኢንጂነር ዘውዴ ወንድሙ በበኩላቸው የከተማው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ በ350 ሚሊዮን ብር መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ዋጋ መጨመር፣ በኃላፊዎች መቀያየርና የግንባታ ተቋራጩ በሆነው ኦሮሚያ ውሀ ስራዎች ድርጅት ድክመት መጓተቱን ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የመልካም አስተዳደር ችግር ታክሎበት ግንባታውን ለማጠናቀቅ መንግስትን 250 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጭ መዳረጉን ገልጸዋል፡፡

"ለፕሮጀክቱ ግንባታ መጓተት ተጠያቂ የሆኑ የቀድሞው የኦሮሚያ ውሃ ስራውች ድርጅት የሥራ ኃላፊች በኪራይ ሰብሳቢነት ተጠርጥረው ለህግ እየቀረቡ ነው" ብለዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር ዘውዴ ገለጻ የክልሉ መንግስት አጠቃላይ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የመደበለት ይህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ በአሁኑ ወቅት 91 ነጥብ 6 በመቶ ደረጃ ላይ ደርሷል።

"ፕሮጀክቱ የዲዛይን ችግር የለበትም" ያሉት አማካሪው የግንባታ ስራው በመጪው ሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ ሥራ ሲጀምር ለ60 ሺህ የነገሌ ከተማ ነሪዎችና በዙሪያው ለሚገኙ የህበረተሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም