በአዲስ አበባ ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ የፅዳት ዘመቻ ተካሄደ

71

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 በአዲስ አበባ ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ "የእግር ጉዞ በማድረግና ቆሻሻዎችን በማንሳት ወደ ሃብት እንቀይር" በሚል መሪ ሃሳብ የእግር ጉዞና የፅዳት ዘመቻ ተካሄደ።

የፅዳት ዘመቻው የተካሄደው የከኢንቫይሮመንታል ፎረስት ቸሪተብል ሶሳይቲ የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ፣ከቂርቆስ፣ቦሌና የካ ክፍለ ከተሞች ጋር በመተባበር ነው።

በዘመቻው ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው በጉለሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ 7 ነዋሪ ወይዘሮ ብርቱካን ሃይለማርያም እንዳሉት እርሳቸውን ጨምሮ 95 እናቶች ደረቅ ቆሻሻዎችን ወደ ብስባሽነት በመቀየር ለአትክልት ልማት እየተጠቀሙ ናቸው።

ከሚሰበስቡት ቆሻሻ የሚበሰብሰውንና የማይበሰብሰውን በመለየት ለጽዳት ባለሙያዎች በማስረከብ ቆሻሻ በአግባቡ የመሰብሰብና የመለየት ተግባር እያከናወኑም እንደሆነም ነግረውናል።

"ቆሻሻን በአግባቡ ጥቅም ላይ ካዋልነው ሃብት እንጂ ጉዳት የለውም" የሚሉት ወይዘሮ ብርቱካን ወረቀትና ፕላስቲኮችንም መልሶ በመጠቀም ሃብት ማመንጨት እንደሚቻል አረጋግጠዋል።

ህብረተሰቡም ይህን በቅጡ ተገንዝቦ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድና ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለበት አሳስበዋል።

የ"ኢንቫይሮመንታል ፎረስት ቻሪተብል ሶሳይቲ" መስራች አቶ ታምሩ ደገፋ ድርጅታቸው ከተመሰረተበት ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ አንዱ ቆሻሻን እንደ ችግር ሳይሆን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ወደ ሀብት የመቀየር ተግባር የሚል እሳቤ በመያዝ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችና ትምህርታዊ ጉዞዎችን እያካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የሆነው የፅዳት ዘመቻም ቆሻሻን እንደ ሀብት በአግባቡ ከተገለገልንበት ለህዝቡ የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚችል ለማስገንዘብ እንደተዘጋጀ ጠቅሰዋል።

የማይበሰብሱ ቆሻሻዎች በተለይም በፕላሰቲክ ቤት የመስራት የሙከራ ስራ እንዳለና ይህም ተግባር ወደ ፊት በስፋት እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ፅዳት የጽዳት ባለሙያዎችና የመንግስት ድርሻ ብቻ ሳይሆን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የበጎ አድራጊ ሰዎችም ድርሻ ነው ያሉት አቶ ታምሩ

መዲናዋ አረንጓዴና ንጹህ እንድትሆን የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ መዲናዋ በእድገቷ ልክ የሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻም እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም በአወጋገድና አጠቃቀም ላይ በትብብር መስራት ካልተቻለ ከሃብትነቱ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ ኤጀንሲው የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር እሸቱ ገለፃ "እኔ አካባቢዬን አጸዳለሁ!! እናንተስ….?" በሚል መሪ ሃሳብ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተጀመረው የፅዳት ንቅናቄ ቀጣይነት እንዲኖረው ይደረጋል።

ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ግለሰቦች የመንግስት ሃላፊዎችና የመዲናዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም