የህዝብ ለህዝብ የባህል ቡድኑ ቆይታ ሲመዘን

98


በሃብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

በጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ቀመር ባለፈው አመት ነሃሴ ወር ላይ ከ350 በላይ ደቡብ ኮሪያውያን ከ70 አመታት በላይ ተለይተዋቸው የቆዩ ቤተሰቦችን ጋር ለመገናኘት ወደ ሰሜን ኮሪያ ያቀኑበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። ሁኔታው የበርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ይዞ ለወራት ዘልቋል። አንዲት ከደቡብ ኮሪያ የተነሱ እናት ሁለት በሰሜን ኮሪያ የሚኖሩ ሴት ልጆቻቸውን ከ70 አመታት መለየት በኋላ ሲያገኟቸው ምን አይነት ስሜትን በሌሎች ሊያሳድር እንደሚችል አስቡት። በወቅቱ ኪም ሁዋክግ ሆ የተባለ ደቡብ ኮሪያዊ ለጋርዲያን ወንድሙን ለማግኘት ያሳለፈውን ውጣ ውረድ እና ከዚያም በኋላ በተገኘው ዕድል ወንድሙን ሲያገኘው ዳግም የመፈጠርን ያህል እንደቆጠረው  አጫውቶታል።

በወቅቱ የኮርያውያኑ ቤተሰቦች ከግማሽ ክፍለ ዘመናት በላይ ለሆኑ ጊዜያት ተለያይተው ዳግም መገናኘታቸው የፈጠረውን ስሜት መገናኛ ብዙሃኑ ለማጉላት ያደረጉትን ጥረት ያህል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የሁለቱ ሃገራት ህዝቦችን የመቀራረብ ፍላጎትና ምኞት እንዲንር አድርጎታል። አንድ አይነት ባህልና እሴት ባላቸው ህዝቦች መካከል የሚኖር ቅራኔ የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅ እንኳን በህዝቦቹ መካከል ውስጥ ለውስጥ የመፈላለጉ ነገር ስለሚያይል ዳግም ለመታደስ የትኛውም አይነት አቀበት፣ ምንም አይነት ርዕዮተ አለም ሊያስቆመው እንደማይችል አለማችን በተለያየ ጊዜያት አሳይታናለች።

ከሁለት አስርተ አመታት መለያየት በኋላም ኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ዳግም ሊገናኙ የቻሉበትን አጋጣሚም በርካቶቹ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡት፣ ሲያነሱትና ሲጥሉት የከረመ ጉዳይ ነው። እንደ ኮሪያውያኑ ወንድማማች ህዝቦች ሁሉ የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች ለዘመናት የነበራቸውን መነፋፈቅ ሲገናኙ ስሜታቸውን የገለፁበት ሁኔታም ከእዝነ ህሊናችን ሊጠፋ የማይችል የትውስታ ማህተም አስቀምጦ አልፏል።

ከተፈጠረው የመነፋፈቅ እንዲሁም ናፍቆትን የመወጣጣት ሂደት በዘለለ ሃገራቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛል። የኤርትራ የባህልና የህዝብ ለህዝብ ልዑክ በሃገራችን የሳምንት ቆይታ በማድረግ ወደ ሃገሩ ተመልሷል።

‘ኪነጥበብ ለማህበረሰብ ያለውን ፋይዳ ለማሳየት እንግዲህ ከዚህ የተለየ ሁነት ከየት ማግኘት ይቻላል! የኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ባህል ቡድን ልዑክ በአዲስ አበባ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎለታል። የባህል ቡድኑን ለመቀበል በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የተገኘው እውቁ ድምፃዊ ንዋይ ደበበ ከኤርትራ አርቲስቶች ጋር ለጋራ አላማ መሰለፍ ደስታ እንደሚሰጠው ተናግሯል። በሁለቱ ሃገራት መካከል ብዙ የመከራ ጊዜ ማለፉን የገለፀው ንዋይ ደበበ አሁን ጊዜው ለፍቅር ቦታ የሚሰጥበት መሆኑን አንስቷል።

በርካታ አንጋፋና ወጣት አርቲስቶችን ያቀፈው የኤርትራ የባህል ቡድን ለህዝብ ስሜት ቅርብ በሆነው ኪነጥበብ የሃገራቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ትርጉም እንዲኖረው አድርጎታል። ኤርትራውያኑ አርቲስቶች ሁለቱ ሃገራት የጀመሩት የሰላም ጉዞ የተቃና እንዲሆን በጥበብ ለማገዝ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የገለፁበት አጋጣሚም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እየጠነከረ እንደሚሄድ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

ሚናስ በላይ ወጣት አርቲስት ነው። ከዚህ ቀደም በካሴት አለፍ ሲልም በሲዲ ድምጻቸውን በመስማት ሲያደንቃቸው ከነበሩ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ጋር መገናኘቱ ትልቅ ደስታን እንደፈጠረለት ተናግሯል። የባህል ቡድኑ በባህርዳር፣ በአዳማና በሃዋሳ ዝግጅቱን ያቀረበ ሲሆን በሄደበት ሁሉ ደማቅ የህዝብ ፍቅርና አቀባበል አልተለየውም።

በዕውቁና አንጋፋው አርቲስት በረከት መንግስተአብ የተመራው የባህል ቡድኑ በባህር ዳር በነበረው ቆይታ የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎችን ከማቅረቡ በዘለለ ከክልሉ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ሰፋ ያለ የውይይት ጊዜ ነበረው። የኢትዮያና የኤርትራ ህዝቦች በታሪክ የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የተነሳ ሲሆን ከሁሉም ጉዳይ ገዝፎ የተነሳው በደብረ ማርቆስ የኤርትራዊ ጎረቤታቸውን ቤት ከ20 አመታት በላይ ጠብቀው ያስረከቡበት አጋጣሚ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በተግባር መገለጫ ሊሆን እንደቻለ ነው።

የህዝብ ለህዝብ የባህል ቡድኑ ሌላ ደማቅ አቀባበል የጠበቀው ደግሞ አዳማ ከተማ ሲገባ ነው። እዚህም የሃገራቱ ህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው የሚያሳይ አቀባበል በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎችና በአባ ገዳ አዳራሽ ተደርጎለታል። በጥንታዊው የኦሮሞ ገዳ ስርአት ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉትና ለስርአቱ ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት ኤርትራዊ ምሁር ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ በአቀባበል ስነ ስርአቱ ወቅት ክብር ተሰጥቷቸዋል። የጥንት የእኩልነት ስርአት አባት በሆነው በኦሮሞ ህዝብ መካከል መገኘታቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው የተናገሩት የባህል ልዑኩ መሪ አቶ ሚካኤል ተፈሪ የጦርነትና የመራራቅ ዘመን ተሽሮ በምትኩ የሰላም፣ የእርጋታና የመልካም ጉርብትና ዘመን የመምጣቱን መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኪነ ጥበብ ስራቸውን በሃዋሳ ሲዳማ አደራሽ ባቀረቡበት ወቅት የኤርትራ የባህል ቡድን የአጨፋፈር ስልት በደቡብ ክልል ከሚገኙ አንዳንድ ብሄር ብሄረሰቦች አጨፋፈር ጋር የነበራቸው ተመሳስሎ የሃገራቱን ህዝቦች የባህል መወራረስ ከትግርኛ ዘፈን የዘለለ እንደሆነ አሳይቶ አልፏል።

በሶስቱም ከተሞች የተደረገላቸው አቀባበል ሞቅና ደመቅ ያለ እንደነበር የገለፀችው ድማፃዊት ሳምራዊት ሃይሌ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በሙያዋ ለማጎልበት ዕድሉን በማግኘትዋ ደስተኛ እንደሆነች ተናግራለች።

በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ማሳረጊያውን ያደረገው የቡድኑ የኢትዮጵያ ቆይታ በበርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የታጀበ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች የተገኙበትም ነበር። የባህል ቡድኑ በሃገራችን የነበረው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር በተገኙባቸው ከተሞች የህዝቡ አቀባበልና የባህል ለባህል መጋራቶች ምስክሮች ናቸው።

በኤርትራውያኑ የህዝብ ለህዝብ የባህል ቡድን አባላት የተጀመረው የህዝቦች ግንኙነት ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላም ከኢትዮጵያ በሚጓዝ ተመሳሳይ የህዝብ ለህዝብ ቡድን የኪነጥበብ ስራውን በኤርትራ አስመራ እንደሚያቀርብም ይጠበቃል። ኪነጥበብ በትክክል ለህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ለተጠናከረ ማህበረሰባዊ መስተጋብር ውሎ ማየት ከዚህ የበለጠ ማሳያ ሊኖረው አይችልምና የበለጠ ይጠንክር እንላለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም