የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅነት መጠናከር በኢኮኖሚና ፖለቲካው ዘርፍ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተጠቆመ

83

ሀዋሳ  የካቲት 16/2011 የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅነት መጠናከር ከህዝብ ለህዝብ ትስስሩ ባለፈ ሁለቱ ሀገሮች በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፍ የሚኖራቸውን ግንኙነት እንደሚያሳድገው ተጠቆመ።

የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የባህል ልዑኩ ቡድን  ባህላዊና ዘመናዊ የሙዚቃ ትርኢቱን በቅርቡ በሃዋሳ ከተማ ተገኝቶ ማቅረቡ ይታወሳል። 

የልዑክ ቡድኑ አባላትና በኪነጥበብ ዝግጅቱ ላይ የተገኙ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት ከሃያ ዓመታት ቆይታ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ወዳጅነት መመስረታቸው ፋይዳው ከፍተኛ ነው።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ባህል ልዑክ ቡድኑ አባል ኢንጅነር አስገዶም ወልደሚካኤል እንዳሉት የአገራቱ መልካም ግንኙነት መመስረት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ከማጠናከር ባለፈ በኢኮኖሚው መስክ በጋራ ለማደግ ያስችላል።

"በእዚህ ዘመን ጦርነት አያስፈልግም፤ እኔ በዕድሜዬ ለረጅም ዓመታት ጦርነት አይቻለሁ፤ ጦርነት ያወድማል እንጂ አሸናፊም ተሸናፊም የለውም" ያሉት ኢንጂነር አስገዶም ጦርነት ህዝብና የሀገር ኢኮኖሚን ስለሚጎዳ የአሁኑ ትውልድ ከእዚህ ሊማር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከጦርነት ይልቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት ለህዝቦች ጠቃሚ በመሆኑ የሁለቱ አገራት መሪዎች ለእዚህ ይበልጥ አተኩረው እንዲሰሩ አመልክተዋል።

የኤርትራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ባህል ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ሚካኤል ተፈሪ በበኩላቸው ሰላም የተገኘው በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብና መሪዎች መካከል ብዙ ጥረት በመደረጉ መሆኑን አስታውሰዋል።

በቀጣይ የተገኘውን ሰላም የማጠናከር ሥራን ጨምሮ ሀገራቱ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ከኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፈ ለአካባቢው ሀገሮችም የሚጠቅሙ መሆን እንዳለባቸው አቶ ሚካኤል ጠቁመዋል።

ከምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ አካባቢ እንድመጡ የተናገሩት አቶ ጎፋ ጎቤ በበኩላቸው ኤርትራና ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም አንድ የነበሩና በጋራ የሚኖሩ ህዝቦች ነበሯቸው።

ከበርካታ ዓመታት መለያየት በኋላ በአሁኑ ወቅት ዳግም ወደሰላማዊ ግንኙነት መምጣታቸው እርስ በርስ ተደጋግፎ ልማትን ለማምጣት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በውጪ ጉዳይ ሚንስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል በበኩላቸው እንዳሉት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያስችላል።

እንደ አምባሳደር ሙሉጌታ ገለጻ አገራቱን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ወደ ኤርትራ፤ ኤርትራውያን ባለሀብቶችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ በሁለቱ ሀገራት መንግስታት በኩል ክፍተኛ ፍላጎት አለ።

"የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትትራ በረራ መጀመሩን ተከትሎ የኤርትራ አየር መንገድም በሳምንት ሦስት ቀን ወደ ኢትዮጵያ በረራ መጀመሩ እንዲሁም የምጽዋ ወደብ ለኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለእዚህ ትልቅ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም