የካቲት ዛሬን ለማለፍና ነገን ለማበጀት ልምድ የሚወሰድበት ወር

71

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 አንዳንድ ወራትና ቀናት የአገሮችን ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ፣ ታሪክ ይቀይራሉ፤ ዘመን ተሻጋሪ አሻራ አሳርፈው ሲያልፉ በትውልድ ይዘከራሉ።

ወርኃ የካቲት "የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ ናቸው"  የሚባሉትን አጼ ቴዎድሮስን እና ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱን አንግሷል፤ ከጦረኞቹም ግራኝ አህመድንና ራስ አሉላ አባ ነጋን አሳርፏል።

30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጅምላ በአካፋና በዶማ በግፍ የተጨፈጨፉት በወርኃ የካቲት ነው። የ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በሽሬ፣ በተንቤን እና በአምባራዶም የጦር ሜዳዎች የተከለከለ መርዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተርከፍክፎ እንዲቃጠሉ መደረጉም የታሪክ ድረሳናት እማኝ ናቸው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በወርኃ የካቲት ለጥቁር ህዝቦች ቀንዲል የሆነውን የጣሊያን ወረራን በአድዋ፣ የሶማሊያ ጦርነትን በካራማራ እንዲሁም የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትን በባድሜ ድል የተቀዳጀችበት ነው። 

በወርኃ የካቲት ጀምበር ገበሬዎች በአጼ ኃይለሥላሴ ላይ አምጸዋል። እንዲሁም መምህራንን፣ ተማሪዎችን፣ አሽከርካሪዎችን፣ የመንግስት ሠራተኞችን፣ የእስልምና ሐይማኖት ተከታዮችንና ወታደሮችን ለተቃውሞ ወደ አደባባይ አስወጥቷል- ሕዝባዊ አብዮትም ቀስቅሷል።

የታሪክ ተመራማሪ ዶክተር አልማው ክፍሌ እንዳሉት፤ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ገበሬ የሆነባት ኢትዮጵያ ካሏት 13 ወራት መካከል ወርኃ የካቲት ለገበሬው ጥጋብ፣ ለመንግስታት ደግሞ የግብር መሰብሰቢያ ወር ነው።

ወርኃ የካቲት ምርት ተሰብስቦ ጎተራ የሚገባበት ወቅት እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪው፤ 'በግብር ገብር አልገብርም' በሚል ግብግብ የገበሬ አመጽ የታየበት ወር መሆኑን ያወሳሉ።

በሌላ በኩል ወቅቱ ተማሪዎች ከአንደኛው መንፈቅ ዓመት ወደ ሁለተኛው የሚሸጋገሩበት በመሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 'መሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ፣ የኃይማኖትና የብሔር ጥያቄዎች' ያነሱበትና አብዮት የቀሰቀሱበት እንደነበር ዶክተር አልማው ይናገራሉ።

የገበሬዎቹ አመጽም ሆነ የ1966ቱ የተማሪዎች ንቅናቄ በስሜት እንጂ በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ ያልተካሄዱ በመሆናቸው የታለመላቸውን ግብ ያልመቱ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ተመራማሪው ያስረዳሉ።

ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ በበኩሉ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችን ያስተናገደው ወርኃ የካቲት በ1966ቱ የተማሪዎች ንቅናቄ ለሦስት ሺህ ዓመታት የዘለቀውን ዘውዳዊ ስርዓት ቢገረስስም አገሪቷ እስከ ዛሬ ድረስ መረጋጋት እንዲሳናት ምክንያት እንደሆነ ያብራራል። 

የፖለቲካ ግለት፣ አመጽ፣ አብዮት፣ የድልና የግፍ ሁነቶች በታሪክ ማህደር የተመዘገቡበት ወርኃ የካቲት ዛሬን ለማለፍና ነገን ለማበጀት ልምድ የሚወሰድበት አስተማሪ ወር ነው። 

የአገር ድንበር በመድፈር የሚቃጣ ወረራን በመቀልበስ ነጻነትን ለማስከበር የተኮራረፈ ሁሉ በወኔ ለትግል የወጣበት ወር እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር አልማው፤ ለአገር፣ ለሰንደቅ ዓላማ፣ ለአንድነትና ለብሩህ አመለካክት ከወርኃ የካቲት በርካታ "ልምዶች መውሰድ ይገባል" ብለዋል። 

የካቲት 12 እና 23ን ለአብነት የሚያነጻጽረው ጋዜጠኛ ጥበቡ፤ ከሁለት ተጻራሪ ታሪካዊ ሁነቶች መማር እንደሚገባ ነው የሚገልጸው።

ፋሽስት ጣሊያን ከአድዋ ድል 40 ዓመት በኋላ ባደረገው ዳግም ወረራ በየካቲት 12 ግፍ ተፈጸመ፣ ከዳግማዊ  አጼ ምኒልክ በኋላ በእቴጌ ጣይቱና በሸዋ ነገስታት መካከል የተደረገ መከፋፈል፣ ልጅ ኢያሱ በማዕከላዊ መንግስት ተቀባይነት ማጣት፣ በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱና በሸዋ ነገስታት መካከል የነበረ ሽኩቻ እንዲሁም በንጉስ ተፈሪ ዘመን የተደራጀና ጠንካራ መንግስት ባለመመስረቱ  መከፋፈል ተፈጥሯል።

በመሆኑም የአንድነትና የአገር ፍቅርን ከ1888ቱ የካቲት 23 የአድዋ ድል፣ የመከፋፈል ዕጣ ፋንታ ደግሞ ከ1929ኙ የካቲት 12 ልምድ መውሰድ እንደሚገባ ይናገራሉ።

"የመላው አፍሪካውያን ድል ነው" ተብሎ በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና የኢትዮጵያዊያን የአንድነት ጥንካሬ መገለጫ የአድዋ ድል የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ትውልድን በሚያስተሳስር የአንድነት መንፈስ እንዲሆን ነው አጽንኦት የሚሰጠው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም