በኢትዮጵያ የባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍን ለማሻሻል ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል

110

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 በኢትዮጵያ የባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍን ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን የባዮ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ባዮ ቴክኖሎጂን በሚመለከት አውደ ጥናት አካሄዷል።

በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በኢትዮጵያ የሰለጠነ የሰው ሀይልና የተደራጀ መሰረተ ልማት ያለመኖር ፣ የባዮ ቴክኖሎጂ መረጃ ውስንነት እንዲሁም ለዘርፉ የፋይናንስ ድጋፍ አለማድረግና ያልተጠናከረ የማበራተቻ ስርዓት መኖሩ ለዘርፉ ችግር የሚፈጥሩ ምክንያቶች ናቸው።

የምርምርና ስርጸት ስርአቱም ችግር ፈቺና ገበያ ተኮር አለመሆኑ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩም የአገሪቷን የልማት ፕሮግራሞችና የቴክኖሎጂ ፍላጎት መሰረት ባለማድረጉና የአገሪቷ እምቅ የብዝሃ ህይወትና ነባር እውቀት በዘመናዊ ባዮቴክኖሎጂ አለመደገፉም ሌላው ማነቆ ነው እንዲሁ።

በሌላ በኩል በአገሪቷ የሚከናወኑ የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት የተበታተነ መሆኑ፣ የመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በመስኩ ተቀናጅተው አለመስራት፣ የገበያ ትስስር ደካማ መሆንና ቴክኖሎጂውን ከውጭ አገር አስገብቶ ለማላመድ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ቅንጅትና ትስስርም ዝቅተኛ መሆን ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም እነዚህንና መሰል ችግሮችን በመፍታት ዘርፉን በአገሪቷ በተገቢው መልኩ ለማሳደግና ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ገልጸዋል።

ይህም የባዮቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት በግብርና፣ በጤና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአካባቢና ተዛማጅ ዘርፎችም በማስፋፋት ጥራት ያላቸው የባዮ ቴክኖሎጂ ምርቶችና አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ በማቅረብ አኗኗሩን ማሻሻልና ለአገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ አስተዋጽኦ ለማድረግ ታስቦ መሆኑ ታምኖበታል።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ለማሳለጥና ለዘርፉ ምርምርና ልማት አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ ሥርዓት ለመዘርጋት በዘርፉ ተገቢው የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖርና እንዲተገበር ማድረግ ተገቢ ነውም ብለዋል።

ፓሊሲው የምርምርና ልማት ትግበራ ብዝሃ ሕይወትና የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮችን ያማከለ እንዲሆን ለማድረግም ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም ላይ እንደ አሜሪካ፣ አውሮፓና ኢስያ የሚገኙ አገራት በባዮ ቴክኖሎጂ ውጤቶች በግብርና፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪና ሌሎችም ህዝባቸውን ተጠቃሚ ከማድረጋቸውም ባሻገር ለአገራቸው የውጭ ምንዛሪም ትልቁ ምንጭ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም