የሞርካ፣ ግብጫ፣ ጨንቻ የገጠር ከተሞችን የሚያገናኝ የ73 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ መሰረት ተቀመጠ

101

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 የሞርካ፣ግብጫ፣ ጨንቻ የገጠር ከተሞችን የሚያገናኘው የ73 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ለማስጀመር ዛሬ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የአስፓልት መንገዱን በባለቤትነት የሚያሰራው ሲሆን 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታልም ተብሏል።

የመንገድ ግንባታውን ስራ 'ቤጂንግ አርበን ኮንስትራክሽን ግሩፕ' የተባለ የቻይና ኩባንያ በተቋራጭነት የሚሰራ እንደሆነ ነው ለማወቅ የተቻለው።

የመንገዱ ግንባታ ሶስት ዓመት ከስድስት ወር የሚፈጅ ሲሆን የመንገዱ መሰራት ለአካባቢው ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከፍ ከማድረግ አንጻር ሚናው የጎላ ነው።

የመሰረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የመንገድ ግንባታው ለወጣቶች ተጨማሪ የስራ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በአካባቢው የሚመረቱ አይነት ብዙ ምርቶች የገበያ እድል የሚያሰፋ ሲሆን የህብረተሰቡን ሰፊ የማምረት ፍላጎት ከመጨመር አንጻርም ሚናው ከፍተኛ ነው ያሉት።

የማማከሩን ስራ ኢትዮጵያዊው ኮር ኮንሰልቲቭ የሚተገብረው እንደሚሆንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

መንገዱን ላለፉት 30 ዓመታት የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሰራለት ውትወታ ቢያደርግም ቀኑ ደርሶ ዛሬ ላይ የመንገዱ ስራ በመጀመሩ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክርላቸው የአከባቢው ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

በተጨማሪም ያመረቱትን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ አቅርበው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከመደገፍ ባሻገር በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግም እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ የመንገዱ ግንባታ በይፋ በመጀመሩ የላቀ ደስታ እንደተሰማቸውም ገልጸዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም