በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ለማህበራዊ ንግድ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል-ጥናት

61

አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአገሪቷ እየተከናወኑ የሚገኙት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በማህበራዊ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሐብቶችን ተስፋ ከፍ ማድረጉን ሮይተርስ ዘግቧል።

ከሚያዝያ 2010 አንስቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው ማሻሻያ ኢንዱስትሪዎችን ፣ቴሌኮምን እና በመንግስት የተያዙ የኃይል ማመንጫ ዘርፎችን ለግሉ ባለሃብት ክፍት ማድረግን ያካትታል።

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት በባለቤትነት ያከናውነው የነበረውን የሎጀስቲክ ዘርፍ በውጭ የገንዘብ ድጋፍ እንዲከናወን ለማስቻል ማሻሻያዎችን ያጠናቀቀ ሲሆን የማዕድንና ነዳጅ ሃብት ማልማትን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በማድረግ እየሰራ ነው።

በኢንቨስትመንት ተጽእኖ ላይ ጥናት የሚያከናውነው የ'ሬኔው ስትራቴጂ' ዋና ስራ አስፈጻሚ ማቲው ዴቪስ ተቋሙ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የማህበራዊ ንግድ ላይ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ስራ አስፈጻሚው 100 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ያልተነካ ገበያ እንዳላት ጠቅሰው፤ ህዝቦቿ ማህበራዊ ተቋማት የሚሰጧቸውን ምርቶችና አገልግሎቶች በብዛት እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

“በኢትዮጵያ ያለው ፈተና ከበድ ቢልም ያሉት አማራጮችም በዚያው ልክ ከፍተኛ ናቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ስትሆን አሁን ኢኮኖሚዋን ክፍት በማድረግ ላይ ነች” ሲሉም ትናንት ናይሮቢ ላይ በተከናወነው "ሳንካልፕ አፍሪካ ፎረም" ላይ ተናግረዋል።

በፎረሙ ላይ ባለሃብቶች፣ የማህበራዊ ንግድ ስራ ፈጣሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ተሳትፈዋል።

“አሁንም ነገሮች ከዚህ በሰፋ መልኩ ይለወጣሉ በማለት እየጠበቅን ነው፣ ነገር ግን ካለፈው ዓመት አንስቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተከናወኑ የሚገኙት ለውጦች በጣም አመርቂ  ስለሆኑ እኛም በዚህ በጣም ተደንቀናል” ሲሉም ተናግረዋል።

“በአገሪቷ አትራፊ የሆኑና ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ ንግዶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ ነው፤ ለዚህ ስኬት ወጣቶችና ሴቶች ማህበራዊ ስራ ፈጣሪ በመሆን የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ነው” በማለትም ነው ማቲው ዴቪስ የሚናገሩት።

በኢትዮጵያ የውሃና የንጽህና አገልግሎት፣ ጤና፣ ትምህርትና የቤቶች ልማት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ፈር ቀዳጅ ሆነው የሚንቀሳቀሱ 50 ሺ የሚጠጉ ኩባንያዎች መኖራቸውን ብሪቲሽ ካውንስል ያሰራው ቅኝት እንደሚያሳይ ሮይተርስ ጠቅሷል።

ኩባንያዎቹ አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት ላይ ቢሆኑም በፋይናንስ እጥረት  ወደ ኋላ እየተጎተቱ መሆኑንም አልሸሸገም ሪፖርቱ።

“40 በመቶ የሚጠጉት ማህበራዊ ኢንተርፕራይዞች ምንም ዓይነት የሚመለስ ወይም የማይመለስ የውጭ የፋይናንስም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ እንደማያገኙ ቅኝቱ ማሳየቱን” በብሪቲሽ ካውንስል የኢትዮጵያ ምክትል ተጠሪ ወሮይዘሪት ውበት ግርማ ተናግረዋል።

ውስን የሆነውን ካፒታል ማዳረስ ቀዳሚው የፋይናስ ተግዳሮት መሆኑን በተቋማቱ ላይ የተደረገው ቅኝት እንደሚያሳይም አሰታውቀዋል።

በአገሪቷ እየተከናወነ ያለው ማሻሻያ ማህበራዊ ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ የሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶቸን የሚጋብዝ መሆኑ ጥሩ ማነቃቂያ ነውም ብለዋል።

ዘርፉን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ከማድረግ ባለፈ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ዘርፉን ለማበረታታት ማህበራዊ ንግዶችን የሚገዛ አውታርና አዲስ ፖሊሲ ማዘጋጀት እንዳለባቸውም ስራ ፈጣሪዎቹ ጠይቀዋል።

“የመንግስት ኃላፊዎች የግል ዘርፉን በደንብ አልተገነዘቡትም፤ እንዲሁም ማህበራዊ ኢንተርፕራይዞች ምን እንደሆኑ አያውቁትም” ሲሉ ነው የጠብታ አምቡላንስ ፕሬዝዳንት ክብረት አበበ የሚናገሩት።

ለማህበራዊ አገልግሎት ሰጪዎችም የታክስ ማበረታቻና ብድር ሊመቻች ይገባልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝብ ቢኖራትም ከኬንያና ኡጋንዳ አንጻር ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪዎች ወይም ተጽእኖ አሳዳሪ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ወደ ኋላ መቅረቷን ዘገባው ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም