የቤንዚን እጥረት በሥራና በኑሯችን ላይ ጫና እየፈጠረ ነው---የድሬዳዋ አሽከርካሪዎች

59

ድሬዳዋ የካቲት 16/2011 የቤንዚል እጥረት በስራና በኑሯቸው ላይ ጫና እያሳደረሰባቸው በመሆኑ መንግስት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ የድሬዳዋ አሽከርካሪዎች   ተናገሩ።

የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባና የንግድና ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

በድሬዳዋ ቤንዚን ለመቅዳት በነዳጅ ማደያዎቹ ረዣዥም የታክሲ ሰልፍ ማየት የተለመደ ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡

በታክሲ ማሽከርከር  የተሰማሩ ወጣቶች ችግሩን አስመልክተው ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ሁለት ወራት የቤንዚን እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ተከስቷል።

የታክሲ አሽከርካሪ ወጣት አስቻለው አየለ ቤንዚን ፍለጋ ከለሊት 7፡00 ሰዓት ጀምሮ እንደሚሰለፍ ተናግሮ " አብዛኛው የሥራ ሰዓት በወረፋ ጥበቃ ስለሚባክን ገቢዬ እየቀነሰ መጥቷል" ብሏል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጀማል ዩኑስ የነዳጅ ማደያዎች ለተወሰኑ አሽከርካሪዎች ከሸጡ በኋላ በጀሪካንና በሌላ መንገዶች በህገ-ወጥ መንገድ ስለሚሸጡ ችግሩ መባባሱን ገልፀዋል፡፡

"ለእጥረቱ መከሰት ሁሉም ማደያዎች በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት ለተጠቃዎች ቤንዚንን መሸጥ አለመቻላቸው ነው" ያሉት ደግሞ ለአመታት በታክሲ ስራ የሚተዳደሩት አቶ አብይ አሰፋ ናቸው፡፡

" ለልጆቻችን ቀለብ ማግኘት አቅቶናል፤ የታሲው ባለቤት ደግሞ ገቢ ይፈልጋል። ገቢ ለማግኘትና ሰዓቱን ለማካካስ ሲፈጠን አደጋ ይከሰታል፤ ችግሩ ውስብስብ ስለሆነ መንግስት መፍትሄ ይስጠን " ብለዋል፡፡

ወጣት ሸምሸዲን አልይ በበኩሉ ችግሩ በከተማው ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ላይ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ መንግስት አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ተኗግሯል፡፡

ያለፉት ሁለት ቀናት ከመጠነኛ ሰልፍ በቀር ብዙም መጨናነቅ አለመኖሩን ግን ተናግረዋል፡፡

"ሰሞኑን ታክሲ ማግኘት ከባድ ሆኗል፤ ምናልባት ከነዳጅ እጥረት ጋር የተያያዘ ችግር ሊሆን ይችላል፤ ሥራ በጊዜ ለመድረስም እየተቸገርን ነው" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ የሺመቤት ተሰማ ናቸው፡፡

የቶታል ከዚራ ነዳጅ ማደያ ባለቤት አቶ ይልማ ብዙነህ በበኩላቸው ማደያዎች የቀረበላቸውን ነዳጅ በሙሉ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ ድረስ እንደሚያድሉ ገልጸው፣ ማደያዎቹ የሚያዙት ነዳጅ በፍጥነትና በወቅቱ አለመቅረቡ ለእጥረቱ መከሰት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማው የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በሙሉ በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት ቤንዚን አስመጥተው ማሰራጨት ቢጀምሩ ችግሩን እንደሚፈታ የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ የኢንዱስትና የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብደላ አህመድ ናቸው፡፡

በዚህ ጉዳይ ለሁለት ጊዜያት ከማደያዎቹ ባለቤቶች ጋር በመወያየት ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

አቶ አብደላ እንዳሉት ህግና ስርዓትን አክብረው ባልሰሩ 3 ማደያዎች ላይ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን አንድ ማደያም ያለበትን የአሰራር ችግር እስኪያስተካክል ድረስ ቤንዚን እንዳያመጣ ታግዷል፡፡

"ማደያዎቹ የሚያዙት ነዳጅ በጊዜና በወቅቱ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ከሚመለከተው አካል ጋር ለመፍትሄው እየተሰራ ነው" ሲሉም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው "ችግሩ ከአቅርቦት እጥረት ብቻ ሳይሆን ነዳጁን በትክክል ካለማደልና ያለአግባብ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ እየተለመደ በመምጣቱ ጭምር የተከሰተ ነው" ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመከላከል ፖሊስ ከታክሲ ማህበራትና ከነዳጅ ማደያዎች ጋር በመቀናጀት የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በእዚህም በአሁኑ ወቅት ችግሩ በአንጻራዊነት እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም