የተበላሹ የእግረኛ መንገዶች ለከተማው ውበት መጓደል መንስኤ እየሆኑ ነው- ነዋሪዎች

104

 አዲስ አበባ የካቲት 15/2011  በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የተበላሹ የእግረኛ መንገዶች የከተማዋን  ገጽታ እያበላሹና ለትራፊክ አደጋ  ምክንያት እየሆኑ ነው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የማዕከላዊ አዲስ አበባ የመንገድ ሃብት አስተዳደር በበኩሉ የቅንጅት ደካማ መሆን መንገዶቹ ተሰርተው ብዙም ሳይቆዩ እንዲበላሹ ምክንያት ሆኗል ነው ያለው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሰለሞን  እንደተናገሩት በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በቅርቡ የተሰሩትና ቀድሞ የነበሩ የእግረኛ መንገዶች በመበላሸታቸው ለእግረኞች ችግር እየሆነ ነው።

በልማትና በተለያዩ ምክንያቶች ተቆፋፍረውና ተቆርጠው የተበላሹ  መንገዶች ቶሎ ባለመጠገናቸው  ምክንያት  የከተማዋን ገጽታ እያበላሹ መሆኑንም አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።

በሜክሲኮ፣ በጊዮርጊስ፣ በቸርችልና በሌሎች አካባቢዎች በልማትና በሌሎች ምክንያቶች ተቆፋፍረው ለእግረኛ ምቹ አለመሆናቸውን መታዘባቸውንም ተናግረዋል።

ከስድስት ኪሎእስከ ሚኒሊክ  የነበረው የእግረኛ መንገድ ለመሰረተ ልማት ግንባታ በሚል ተቆፍሮ መበላሸቱንና እስካሁን  አለመሰራቱን  ለአብነት  የጠቀሰችው ወጣት  ህሊና ሳምሶን  በተለያዩ አካባቢዎች መንገዶቹ  ገና  ከመሰራታቸው ይፈርሳሉ  ብላለች።

በተለያዩ አካባቢዎች ታይልስ ይነጠፍላቸዋል በሚል የተነሱ የእግረኛ መንገዶች ለህብረተሰቡ ምቹ ሁኔታ አለመፍጠራቸውና መፍትሔ እንደሚፈልግም ገልጻለች።  

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ  እንዳሉት በመንገዶቹ መቆፋፈር ምክንያት እግረኛው የመኪና መንገድን እንደ አማራጭ በመጠቀሙ አልፎ አልፎ የትራፊክ አደጋ  ይከሰታል።

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተቆፋፈሩና የተቆራረጡ የእግረኛ መንገዶች  ለትራፊክ እንቅስቃሴው እንቅፋት በመሆናቸው ፈጣን መፍትሔ ሊሰጣቸው  ይገባል  ብለዋል ፡፡

የማዕከላዊ  አዲስ  አበባ የመንገድ  ሃብት አስተዳደር  ዳይሬክተር  አቶ በላይ  ወልደአረጋይ  በበኩላቸው በከተማዋ በግለሰቦችና  በመንግስት ተቋማት ጭምር  ከተቋሙ  እውቅና ውጭ  መንገዶች እየተቆፈሩ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

በርካታ መንገዶች ያለፍቃድ በመሰረተ ልማት ተቋማት የሚቆፈሩና  በግል የሚያጥሩት ግለሰቦች በተለያዩ ግዜ እንዲቀጡ ቢደረግም አሁንም በተፈለገው መልኩ ለውጥ አለመምጣቱን ነው አቶ በላይ የገለፁት። 

የመንገድ ግንባታ ወጭ ከፍተኛ በመሆኑ  መንገዶቹ ሲቆፈሩ አልያም ሲፈርሱ ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላት ፍቃድ እንዳላቸው በማረጋገጥ በኩል  ህብረተሰቡ ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።  

በተለይ የመሰረት ልማት ተቋማት ከሆኑት መብራት ሃይል፤ ቴሌኮምና ውሃና ፍሳሽ ጋር ያለው ቅንጅት  ደካማ መሆኑ ለመንገዶች  መበላሸት  ዋነኛ  ምክንያት እንደሆነ ያመለከቱት  ዳይሬክተሩ  ከተቋማቱ ጋር በቀጣይ በተጠናከረ  ቅንጅት ለመስራት  ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል። 

የከተማዋን የእግረኛ መንገድ  ለማዘመን  ባለፉት  ወራት 14.5 ኪሎሜትር ታይልስ  በመቶ ሚሊዮን ብር መገንባቱን የገለጹት አቶ በላይ በቀጣይ ወራትም አስራ ስድስት የታይልስ ንጣፍ የሚሰራላቸው  መንገዶች ተለይቷል ነው ያሉት።

ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶችን ችግራቸውን በመለየት የማደስ ስራ እየተሰራመሆኑንም ተናግረዋል።  

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥሁማይ ወልደገብርሄል እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ  የእግረኛና ሌሎች መንገዶችን ለመጠገን ከስምንት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ወደ ሥራ ገብቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም