በልግ አብቃይ በሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ዝናብ ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል

95

አዲስ አበባ የካቲት 15/2011 በሚቀጥለው ሳምንት የበልግ አብቃይ በሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከመደበኛው መጠን ጋር የተቀራረበ ዝናብ ይጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በሚቀጥለው ሳምንት በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ይጨምራል ተብሏል።

በዚህም መሰረት በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ኢሉ አባቦራ፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ የአርሲና የባሌ እንዲሁም የቦረናና የጉጂ ዞኖች እና አዲስ አበባ ዝናብ ይኖራቸዋል።

ከዚህም ሌላ  ከአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ምስራቅ ጎጃም፣ እና ደቡብ ጎንደር፣ ከአፋር ዞን 3፣ 4 እና 5 ከመደበኛው የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖራቸው ኤጀንሲው ገልጿል።  

የምስራቅና የደቡብ ትግራይ ዞኖች፣ የከፋና የቤንች ማጂ፣ የወላይታና ዳውሮ፣ የጋሞጎፋ ዞኖች፣ የጉራጌና የሀድያ፣ የሲዳማና የደቡብ ኦሞ አብዛኛው ክፍሎችም በተመሳሳይ ከመደበኛው የተቀራረበ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠቃል።   

ይኸው ዝናብ በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ለሚካሄደው የእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ ፣ ለአፈር እርጥበትና መጠናከር እንዲሁም ለዘር መዝራት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ኤጀንሲው አስታውቋል።

በመሆኑም ገበሬውን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበልግ እርሻ የማሳ ዝግጅትና የዘር መዝራት ተግባራትን ከወዲሁ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኤጀንሲው አሳስቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም