የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ የተቋቋመበት 20ኛ ዓመትና የናይል ቀን ተከበረ

116

አዲስ አበባ የካቲት 15/2011  የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ የተቋቋመበት 20ኛ ዓመትና 13ኛው የናይል ቀን ዛሬ በሩዋንዳ ርዕሰ-መዲና ኪጋሊ ተከበረ።

የናይል ተፋሰስ አገራት የአባይ ወንዝን የውሃ ሃብት በጋራ ለመጠቀምና ለመጠበቅ በታንዛንያ ርዕሰ-መዲና ዳሬሰላም የተመሰረተው የትብብር ማዕቀፍ የናይል ቤዚንኢኒሼዬቲቭ በመባል ይጠራል።

ኢኒሼዬቲቩ ዘንድሮ የተቋቋመበትን 20ኛ ዓመት እና 13ኛው የናይል ቀን "የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ በ20ኛ ዓመት፤ በጋራ ስንሆን ጠንካራ ነን" በሚል መሪ ሀሳብ በሩዋንዳ ርዕሰ-መዲና ኪጋሊ ተከብሯል።

የሩዋንዳ የአካባቢ ሚኒስቴርና የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ በዓሉን በጋራ ማዘጋጀታቸውንም ኢኒሺዬቲቩ አስታውቋል።

የናይል ተፋሰስ አገራት ሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት በቡሩንዲ ርዕሰ-መዲና ቡጁምቡራ ባካሄደው 26ኛ ዓመታዊ ስብሰባው 2019 "የናይል ቤዚን ዓመት" ተብሎ እንዲሰየም መወሰኑንም ይታወሳል።

የአባይ ወንዝ የውሃ ደህንነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለናይል ቤዚን ቀጣና የምግብና የሃይል ዋስትና መጠበቅና በየአገራቱ የሚኖሩ ህዝቦች ያለባቸውን ድህነትን ከማስወገድ አንጻር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተጠቅሷል።

የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካትና የቀጣናውን ትብብር እውን ለማድረግም የአባይ ወንዝ ያለው ሚና ቁልፍ እንደሆነ ተመልክቷል።

የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ ዳይሬክተር ኢኖሰንት ንታባና 2019 "የናይል ቤዚን ዓመት" ተብሎ የተሰየመው የናይል ተፋሰስ አገራት ሁሉም ልማቶች የተያያዙት ከአባይ ወንዝ ጋር እንደሆነ ያለውን እውነታ አገራት እንዲረዱት ነው ብለዋል።

የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ በ20 ዓመት ቆይታው 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባቸው 84 የጋራ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሆነው በናይል ተፋሰስ አገራት ውስጥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ማድረጋቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በየአገራቱ የናይል ቤዚን ኢኒሼዬቲቭን የሚያጠናክሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ እንዲሆኑና የውሃ ሀብትን በጋራ መጠቀምና መጠበቅ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ለአገራቱ ዜጎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውም ተመልክቷል።

12ኛው የናይል ቀን በዓልን ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ "ናይል የጋራ ሀብት - ለዘላቂ ልማት ተባብሮ መስራት" በሚል መሪ ቃል መከበሩ የሚታወስ ነው።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሺዬቲቭ አባል አገራት ቡሩንዲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም