የፈጠራ ስራዎች እንዲለዩና ጥቅም ላይ እንዲውሉ መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል-የፎረሙ ተሳታፊዎች

77

አዲስ አበባ  የካቲት 15/2011 የፈጠራ ስራዎች እንዲለዩና ጥቅም ላይ እንዲውሉ መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ለኢዜአ አስተያየት የሰጡ የስምንተኛው የከተሞች ፎረም የፈጠራ ውጤት አቅራቢዎች ጠየቁ። 

በየክልሎች ተወስነው የሚገኙትን የፈጠራ ውጤቶች መሰብሰብ ፈጠራን ከማበረታት ባሻገር በመላው አገሪቷ ዳብረውና ተሻሽለው እንዲሰራጩ ያስችላል ሲሉም አክለዋል።   

በፎረሙ ላይ የምግብ ማብሰያ የፈጠራ ውጤቶችን ይዞ የቀረበው ወጣት ሲሳይ ጎዳና በርካታ ፈጠራዎች እንዳሉት ተናግሮ በአሁኑ ወቅት ባለው የገንዘብና የሃብት ችግር የፈጠራ ውጤቶቹን ወደ ስራ ማስገባት አለመቻሉን ገልጿል።     

በመሆኑም የፈጠራ ስራዎቹ ለህዝብ እንዲተዋወቁና ምን ዓይነት የፈጠራ ስራ አለ የሚለው እንዲለይ መንግስት በመላው የአገሪቷ ክፍሎች የሚገኙትን ፈጠራዎች የመሰብሰብና ወደ ጥቅም የማስገባት ስራ መስራት ይኖርበታል ሲልም ጠይቋል። 

ይህም ህብረተሰቡ ያሉትን የፈጠራ ስራዎች በመገንዘብ ወደ ተግባር እንዲገቡ የበኩሉን  ያግዛል ብሏል።  

ሌላው የፈጠራ ውጤት አቅራቢ መምህር ተስፋዬ በለጠም ከአካበቢው ከሚገኙ ቁሳቁሶች የላብራቶሪ የተማሪዎች መርጃ መሳሪያ መፍጠር በመቻሉ ለኢግዝቢሽኑ እንደተጋበዘ ተናግሯል።   

የፈጠራ ውጤቶቹ በቀላሉ የሚሰሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በዋጋ በኩልም ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ ጠቅሶ መንግስት በውድ ዋጋ ከውጭ የሚያስገባውን ማስቀረት ያስችላል ሲልም አብራርቷል።   

መንግስት ለፈጠራ ስራዎች የሰጠውን ትኩረት የበለጠ ቢያሻሻልና የፈጠራ ስራዎች የልዕቀት ማዕከል ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ ቢያመቻች የፈጠራ ስራዎቹ የበለጠ የሚዳብሩበትንና ለህብረተሰቡ የሚሰራጩበትን ሁኔታ ዘላቂና አስተማማኝ ማድረግ ይቻላል ሲልም አስተያየቱን አክሏል።

ሌላው የፈጠራ ባለቤት ወጣት ዘለቀ ተስፋዬ ደግሞ የስጋ መክተፊያ ማሽን የፈጠረ ሲሆን ምርቱን ወደ ገበያ ለማውጣት የገንዘብ አቅም እንደሌለው ተናግሯል። 

በመሆኑም መንግስት ብቻ ሳይሆን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የፋይናንስ አቅም ያላቸው ግለሰቦችም የፈጠራ ውጤቶቹ ተሰብሰበውና በስፋት ተመርተው ወደ ገበያ የሚገቡበት ሁኔታ ላይ መስራት ይገባቸዋል ሲል አስተያየቱን አክሏል።    

በ10 ደቂቃ 5 ኪሎ ቡናና ሽንኩርት መፍጨት የሚችል ማሽን የፈጠረው ወጣት አቤኔዘር ጉልማ በበኩሉ የፈጠራ ስራዎችን በዓላትና ኢግዚቢሽኖች ላይ ብቻ ማቅረብ ህብረተሰቡ ያሉትን የፈጠራ ስራዎች እንዲያውቅ ቢያግዙም ሁሉንም ህብረተሰብ ግን መዳረስ አይቻልም ብሏል።   

በመሆኑም ህብረተሰቡ የአገር ውስጥ የፈጠራ ውጤቶችን እንዲጠቀም፣  እንዲያበረታታ፣ ስለ ፈጠራ ውጤቶቹ ግብዓት የሚሆን አስተያየት እንዲሰጥ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት በስፋት ሊሰሩ ይገባል ሲል ገልጿል።  

በጅግጅጋ ከተማ "መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና" በሚል መሪ ሐሳብ ከየካቲት 8 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ሲካሄድ በነበረው የከተሞች ፎረም ላይ በግለሰቦች፣ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተፈጠሩ በርካታ የፈጠራ ውጤቶች ቀርበዋል።

ለዚህም የላቀ የፈጠራ ስራ ላቀረቡ እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣይ ለሚዘጋጀው 9ኛው የከተሞች ፎረም ላይ ተሻሽለውና ጎልብተው ይቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም