በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የሚየደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

132

አዲስ አበባ የካቲት 15/2011 በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆናል።

የፕሪሚየር ሊጉ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ይካሄዳሉ።

ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት 30 የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎች በማሸነፍ 12 ነጥብ ይዞ በአንደኝነት እየመራ ይገኛል።

ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በሊጉ ውጤታማ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን የሊጉን መሪነት ከስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ መረከቡ ይታወሳል።

በአንጻሩ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በስድስተኛው ሳምንት መርሃ ግብር ከከምባታ ዱራሜ ጋር ባደረገው ጨዋታ አቻ መውጣቱን ተከትሎ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ 11 ነጥብ በመያዝ መሪነቱን ለኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስረክቧል።

ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ የያዘውን መሪነት ለማስቀጠል በአንጻሩ ደግሞ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዳግም ወደ መሪነቱ ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ነገ ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከመከላከያ የሚጫወቱ ሲሆን ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከፌደራል ፖሊስ በተመሳሳይ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሰባተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ጎንደር ከተማና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ የማያደርጉ አራፊ ክለቦች ናቸው።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በምድብ ሁለት ዛሬ ጎንደር ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ ጎንደር ከተማ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን 86 ለ 78 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ጎንደር ላይ ሲቀጥል ነገ ጎንደር ከተማ ከሀዋሳ ከተማ እሁድ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በተያያዘ በኢትዮጵያ ወንዶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በምድብ ሁለት ዛሬ ጎንደር ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ ጎንደር ከተማ የካ ክፍለ ከተማን 66 ለ 43 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ነገ በምድብ ሁለት ወልቂጤ ከተማ ከጎንደር ከተማ ከነገ በስቲያ የካ ክፍለ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ 3 ሰዓት ጎንደር ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ሁሉንም ክለቦች በአንድ ምድብ በማካተት በዙር ያካሂድ የነበረውን የውድድር መርሐ ግብር በመቀየር ቡድኖች በሁለቱም ፆታዎች በሁለት ምድብ ተከፍለው በዙር ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት የውድድር መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።

በዚሁ መሰረት በወንዶችና በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በተመሳሳይ ምድብ በሁለት የተደለደሉት ሦስቱ ክለቦች ወደ ጎንደር አቅንተው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ጨዋታ ያደርጋሉ።

የሁለቱም ምድብ ጨዋታዎች ባለፈው ሳምንት መካሄድ የነበረባቸው ቢሆንም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በአንድ ሳምንት አራዝሞት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ጨዋታዎቹ እንዲካሄዱ መወሰኑ ይታወቃል።

በፕሪሚየር ሊጉ በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ ስድስት ቡድኖች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ.ም በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቮል ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም