በአማራ ክልል ከ4 ሚሊዮን በላይ የቡናና የፍራፍሬ ችግኝ እየተተከለ ነው

54

ባህር ዳር የካቲት 15/2011 በአማራ ክልል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በኩታ ገጠም ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የቡናና የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ አወቀ ዘላለም እንዳሉት በክልሉ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞችን በኩታ ገጠም የማልማት ሥራ የተጀመረው በክልሉ አምስት ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ 20 ቡና አብቃይ ወረዳዎች ነው።

ቡና፣ ማንጎ፣ አቡካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ አፕልና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች በኩታ ገጠም በተለዩ የእርሻ ማሳዎች ላይ በመስኖና በመኽር እርሻ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አወቀ እንዳሉት ዘንድሮ ለተከላ የተዘጋጁ ከ4 ሚሊዮን 345 ሺህ በላይ የቡና፣ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞችን በበጋ ወራት መስኖን በመጠቀም በ746 ሄክታር መሬት ላይ የመትከል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ከሚተከሉ ችግኞችም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የቡና ችግኝ ሲሆን ቀሪው የቆላና የደጋ ፍርፍሬ ችግኞች መሆናቸውን አመልክትዋል።

እስካሁንም ከ87 ሺህ በላይ ችግኝ በ55 ሄክታር መሬት ላይ መተከሉን የገለጹት አቶ አወቀ የችግኝ ተከላ ሥራውን በቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ በቅርበት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።   

እየተተከለ የሚገኘው የቡናና ፍራፍሬ ችግኞችም  ከአራት ዓመት በፊት ምርት መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ነው ባለሙያው ያመለከቱት

“ቡናንና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በኩታ ገጠም ማልማት የግብርና ባለሙያ በአንድ አካባቢ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ከሚኖረው ጠቀሜታ በተጨማሪ አርሶ አደሩ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ያስችላል” ብለዋል።

በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የሮቢት ባታ ቀበሌ አርሶ አደር አደለኝ አሻግሬ እንዳሉት በኩታገጠም እርሻ ዘንድሮ 400 የተሻሻለ የቡና ችግኝ በመስኖ ልማት መትከላቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት የበጋ ወራትም ኩታ ገጠም የአሰራር ዘዴን በመጠቀምና የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ በመከተል 600 የቡና ችግኝ ተክለው እየተንከባከቡ ይገኛሉ።

ከአምስት ዓመት በፊት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት የማንጎና አቦካዶ ተክልም በዓመት እስከ 10 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩ ገልጸዋል።

በዚሁ ወረዳ የይጎማ ሁለቱ ቀበሌ አርሶ አደር ተወልኝ ደሌ  በበኩላቸው ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የተሻሻለ ቡናና ማንጎ ከሩብ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ተክለው እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በኩታ ገጠም እርሻ በመስኖና በመኽር የተተከለው ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ታውቋል።

በክልሉ ቡና አብቃይ በሆኑ ወረዳዎች ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል እየለማ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም